ፓትርያርክ ፒዛባላ ‘በጾም ወቅት የምናደርገው ይቅር ባይነት ከኃይለኛ የጥላቻ ቃላት የበለጠ ጠንካራ ነው' አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዐቢይ ጾም መጀመሩን በማስመልከት የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ክርስቲያኖች በተለይም ጦርነት፣ ራስ ወዳድነት እና ዓመፅ በተንሰራፋበት በአሁኑ ወቅት የትንሣኤውን ጌታ እና የዓለምን ተስፋ የሚወክለውን የክርስቶስን ቅዱስ መስቀል እንዲመለከቱ አሳስበዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ለቅድስት ሀገር ምእመናን በላኩት የዐብይ ጾም መልእክታቸው የጥላቻ እና የቂም በቀል ቃላት፣ በትዕቢት የተሞላ የግጭት እና የጥላቻ ንግግር እግዚአብሔር በልጁ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእርቅን ቃል ከመናገር ሊያግደው እንደማይችል እያንዳንዱ የክርስቶስ አማኝ ሊገነዘበው የሚገባ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አዲስ ዕድል
በጾም ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራው ጊዜ የደረሰበትን በደልና ስቃይ ስንለማመድ የጸጋን እና የይቅርታን ስጦታ የመቀበል እድልን እንደሚሰጠን ያስታወሱት ብጹእነታቸው፥ “በዚህ ዓለም እና በዘመናችን ኃያላን እና ጥበበኞች ዘንድ ሞኝነት ሊመስል ቢችልም ይህ የቅዱስ መስቀሉ አዲስ ቃል ያስፈልገናል” ካሉ በኋላ፥ “ይህም ቃል ዓለማዊ የሆኑ መስፈርቶችን በመገልበጥ የተስፋ እና የሰላም መንገዶችን እንደገና መክፈት የሚችለው ብቸኛው ቃል እንደሆነ” በመግለጽ፥ አስተሳሰባቸውን እና አመለካከታቸውን በማደስ የወደፊቱን ጊዜ በሰላም ተስፋ ማድረግ የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
ፓትርያርክ ፒዛባላ “ይህ መንገድ በከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን፣ ነገር ግን በደስታ የምንማረውን፣ አዲሱን የስጦታ እና የይቅር ባይነት አመክንዮ የሆነው የመስቀሉ መንገድ ለመራመድ ዝግጁ የሆኑትን ወንዶች እና ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና አዛውንቶችን፣ ቤተሰቦችን እና ልጆችን አስተሳሰባቸውን እና አመለካከታቸውን ለማደስ ጥሪውን ያቀርባል” ብለዋል።
ሰላም እና እርቅ
ካርዲናሉ በቅድስት ምድር ያሉ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ህማማቱን የሚያስታውሱ ጽሁፎችን ለማንበብ ጊዜ እንዲሰጡ እና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀራንዮ መንገድን እና የመቃብር ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
እርቅ ውጤታማ የሚሆነው ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በንጹህ ልብ ስናገለግል ብቻ እንደሆነ ያስታወሱት ካርዲናሉ፥ “ስጦታው አስማታዊ አይደለም፥ ነገር ግን ይሄን ስጦታ መቀበል፣ መመስከር፣ መኖር እና መካፈል አለበት” ካሉ በኋላ፥ ሁላችንም ማለትም አገልጋዮች እና ምእመናን፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት በጋራ መሳተፍ እንዳለብን ብሎም የማስታረቅን ቃል እና አገልግሎት ወደ ዓለም ለማድረስ በጋራ ሀላፊነት መውሰድ እንዳለብን አሳስበዋል።
የትንሣኤው ምልክት
ፓትርያርክ ፒዛባላ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር በሚታረቁበት ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲታረቁ እና ከዚያም ዕርቁን ለሰው ልጆች ሁሉ እንዲያደርሱ ጥሪው በጥልቅ ሊሰማቸው ይገባል በማለት ምእመናን እንደ ቤተሰብ አንድ ላይ በመሆን እንዲጾሙና እንዲጸልዩ በመጋበዝ፥ “ይቅር ባይነት ስጦታ ሊሆን የሚችለው ከራስ ወዳድነት ጭንቀቶች ነፃ ሲያወጣን እና የሌሎችን ፍላጎት እንድናውቅ ሲያደርገን ነው” ካሉ በኋላ፥ “ይህን በእግዚአብሔር ምህረት የተሰጠንን ጊዜ አናባክን” በማለት ደምድመዋል። “ይህ የዐቢይ ጾም ዝም ብሎ የተለመደ ነገር ብቻ አይደለም፥ እንዲሆን ከፈለግን አዲስ እና የተለየ የዐቢይ ጾም ሊሆን ይችላል! በእርግጥ በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ላይ ያረፈው ይህ ቅዱስ ጊዜ ለዚህች ምድር የመጽናናት እና የማስታረቅ ጊዜ ሊሆን ይችላል” በማለትም አጠናቀዋል።
አባ ፓቶን፡- “ጥላቻ ሞትን እና ጥፋትን አምጥቷል”
የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ፍራንቸስኮ ፓቶን በበኩላቸው በቅድስት ሀገር የሚገኙ ክርስቲያኖችን በእጅጉ የሚጠቅመው ዓመታዊው የ ‘መልካም አርብ መዋጮ’ ላይ ካቶሊካውያን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ የጋበዙበትን የቪዲዮ መልእክት ልከዋል።
አባ ፓቶን በመልዕክታቸው ጦርነቱ በክልሉ ላይ ያስከተለውን መከራ፣ ሞትና ውድመት፣ እንዲሁም በወንድማማቾች እና እህትማማቾች መካከል የከረረ ጥላቻ እንዳስከተለ አስታውሰው፥ “ብዙ ቤተሰቦች ሥራ አጥ ሆነዋል፥ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ወይም ለቅርብ ዘመዶቻቸው ለህክምና ክፍያ ለመክፈል ተቸግረዋል” ካሉ በኋላ፥ “በርካታ ጥንድ ወጣቶች ቤተሰብ የመመሥረት እና ልጆች ለመውለድ የነበራቸውን ህልም ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ተገደዋል” ብለዋል።
የልግስና ጥሪ
በገዳሙ ውስጥ እና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚያገለግሉ መምህራንና የአካባቢው ተባባሪ ሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈል እንዲሁም በግጭቱ ሳቢያ እየደረሰ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ከፍተኛ ትግል ሲደረግ እንደነበር በማስታወስ፥ ቀውሱ እሳቸውንም እንደነካ የቅድስት ሀገር ጠባቂ ካህኑ አመልክተዋል።
አባ ፓቶን አክለውም፥ “ሆኖም ግን በዓለም ዙሪያ ባሉ ክርስቲያኖች ትብብር በኩል እራሱን ለገለጠው ለእግዚያብሔር መለኮታዊ ጥበቃ ምስጋና ይግባውና የበጎ አድራጎት እና ተቋማዊ የሆኑትን በርካታ ኢኮኖሚያዊ ግዴታዎችን ማሟላት ችለናል” ብለዋል።
የቅድስት ሃገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ፓቶን በመጨረሻም በሚያዝያ ወር ውስጥ በሚካሄደው የ ‘መልካም አርብ መዋጮ’ በኩል በቅድስት ምድር የሚገኙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዲያስታውሷቸው በዓለም ዙሪያ ያሉ ክርስቲያኖችን በመጋበዝ፥ “እኛ ሁለንተናዊቷን ቤተክርስትያን ወክለን የቅድስት ሀገርን ቤተ መቅደስ እና በዙሪያቸው የሚኖሩ ክርስቲያኖችን እየተንከባከብን በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት አገልጋዮቻችሁ እኛን እንዳይረሱን አበረታቷቸው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።