ከምስራቃውያን አቢያተ ክርስቲያናት ሰሞኑን የተሰሙ ዜናዎች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከምስራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት የተሰሙ የዚህ ሳምንት አበይት ዜናዎች መካከል፦
ዐቢይ ጾም መጀመሩ
ባለፈው ሳምንት የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የላቲን ሥርዓት ተከታይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አማኞች የዐቢይ ፆምን የጀመሩ ሲሆን፥ በአንዳንድ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ይህ ፆም የሚጀምረው ከሁለት ቀናት በፊት ሰኞ ዕለት እንደሆነ እና በዚህም እስከ ዕለተ ትንሳኤ 48 ቀናት እንደሚፆም ተገልጿል።
በዐቢይ ጾም ወቅት የምሥራቃውያን አቢያተ ክርስቲያን ምዕመናን ከሥጋና ከወተት ተዋጽኦዎች በመራቅ ከመንፈቀ ሌሊት እስከ ቀትር ድረስ ይጾማሉ። በባይዛንታይን ትውፊት መሰረት ዐቢይ ጾም በልዩ ልዩ ሥርዓተ አምልኮዎች የሚከበር ሲሆን፥ ለምሳሌ ሰኞ ዕለት ታላቁ ትእዛዝ የሚታወስበት፣ በዕለተ ሐሙስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስጦታ ለሆነው ሥጋና ደሙ የሚደረግ ሥርዓተ ቅዳሴ፣ እንዲሁም ዕለተ ዓርብ ላይ የ ‘አካቲስት መዝሙር’ ወይም አምላካችንን እና ቅዱሳንን የምናከብርበት ዝማሬ የሚቀርብበት ቀን ነው።
የዩክሬን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪ አቀረበች
“ያለ እውነት እና ፍትህ የትኛውም የሰላም ስምምነት ሊፈረም አይችልም” ያሉት የዩክሬን የግሪክ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳቪያቶስላቭ ሼቭቹክ በቅርቡ በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት አሁናዊ ሁኔታ አስመልክተው ምላሽ ሰጥተዋል።
ሊቀ ጳጳሱ ለምዕመናን ባስተላለፉት ሳምንታዊ የቪዲዮ መልዕክት ዩክሬን ለህልውናዋ እየታገለች መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው በመናገር፥ ዩክሬናውያን ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን እየተጋፈጡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት በጽናት እንዲቆሙ አሳስበው፥ “የዚህን ዓለም ኃያላን አትፍሩ! የዩክሬንን ድል ለማረጋገጥ የተረጋጋ አእምሮ፣ ብልህ ልብ እና ከብረት የጸና ጥንካሬ ሊኖረን ይገባል” ብለዋል።
በዮርዳኖስ አዲስ የተሾሙት ጳጳስ
ብጹእ አቡነ ኢያድ ትዋል በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ በምትገኘው አል-ማግታስ መንደር ውስጥ ባለው የጥምቀተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በተደረገ ታሪካዊ ሥነ ሥርዓት በዮርዳኖስ የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ እና የሃገረ ስብከቱ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፥ ይህም በቅርቡ ተመርቆ በተከፈተው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሾሙ የመጀመሪያው የዮርዳኖስ ሃገረ ስብከት ጳጳስ ያደርጋቸዋል ተብሏል።
የማዕረገ ጵጵስና ሥነ ስርዓቱም በብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የተመራ ሲሆን በበዓሉ ላይ በርካታ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ምዕመናን እንደተገኙ ተገልጿል።