MAP

2020.03.23 Preghiera in famiglia 2020.03.23 Preghiera in famiglia 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮ በቤተሰባችን ውስጥ ያለውን የልብ ስብራት እና ጉዳት መርሳት እንደሚገባ መከሩ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለመጋቢት ወር ያዘጋጁት የጸሎት ሃሳብ የይቅር ባይነትን ጸጋ በመቀበል ቤተሰቦች ፈውስን እንዲሁም እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሰጠውን በረከቶች ለማግኘት እንድንችል በርትተን እንድንጸልይ ይጋብዘናል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የመጋቢት ወር የጸሎት ሃሳብ በችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን የሚያስታውስ ሲሆን፥ ይቅርታ በማድረግ ስብራት ያጋጠማቸው ቤተሰቦች ፈውስ ሊያገኙ እንዲችሉ እንድንጸልይ ያበረታታናል።

እንዲሁም የደረሱብንን ጉዳቶችን በመርሳት ወይም ይቅር በማለት፥ ቤተሰቦች እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሰጣቸውን ስጦታዎች እንዲያገኙ እንጸልያለን። ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር በቤተሰባችን ውስጥ የሰጠንን የበረከት ብዝሃነት እና ሙልአት እንድናውቅ ጸሎት ማድረግ እንዳለብንም ጭምር ይጋብዘናል። የጸሎት ሃሳቡ በቤተሰባችን ውስጥ በረከቶቻችንን የምናስተውልበት ዋነኛው መንገድ እግዚአብሔርን የይቅር ባይነትን ጸጋ መለመን መሆኑን እንድናስብ ይጋብዘናል። በዚህ ጸጋ በእግዚአብሔር እርዳታ ራሳችንን እና ሌሎችን በእግዚአብሔር የተወደዱ ኃጢአተኞች አድርገን መቀበል እንጀምራለን።

በዚህ ወር የሚደረገው ውብ ጸሎት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በድህረ ሲኖዶሳዊ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው በሆነው ‘አሞሪስ ላቲሺያ’ ላይ ቤተሰብን አስመልክተው በፃፉት የግል አስተያየት ላይ በግልጽ ይታያል።

በሃዋሪያዊ ማሳሰቢያቸው ምዕራፍ አራት ላይ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን አስደናቂ የፍቅር መዝሙር ለቤተሰብ እንዴት እንደሚሠራ ያብራሩበት ሲሆን፥ ሃዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልዕክቱ “ፍቅር ይታገሳል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም በደልን አይቆጥርም” ብሏል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቤተሰብ ውስጥ ለሌላ ሰው ድክመቶች እና ስህተቶች ጠንከር ያለ ምላሽ አለመስጠት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያብራሩ ሲሆን፥ የልብ ስብራት ወይም የደረሰብን ጉዳት በልባችን ውስጥ እንዲኖር ብሎም ስር እንዲሰድ እና እንዲያድግ መፍቀድ እንደማይገባ መክረዋል። ሰዎች ስለሆንን በሌሎች በተለይም በቤተሰብ አባል ስንጎዳ ጠንከር ያለ ምላሽ መስጠት እንችላለን። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ግን ያንን ጉዳት እንድንተወው እና ቂም በቀል በልባችን ውስጥ እንዲንሰራፋ እንዳንፈቅድ ቅዱስ ጳውሎስ እንደጋበዘን ያስታውሱናል።

በቁጣ ውስጥ ሆነን ወይም በልባችን ቂም ይዘን ፀሐይ እላያችን ላይ እንዳትጠልቅ፣ ምንም እንኳን በየዕለቱ ሊያጋጥሙን የሚችሉ በርካታ ብስጭቶች ቢኖሩም ቀኑ ከማለቁ በፊት አብሮነታችንን በሆነ መንገድ ለመግለጽ ቤተሰቦቻችንን ለማግኘት መሞከር እንዳለብን ይመክሩናል።

ግን ይህንን ለማድረግ ጥንካሬን ከየት እናገኛለን? ይቅር ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ ከየት እናገኛለን? ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ምን ያህል እንደሚወደን እንድናስብ ጋብዘውናል። እኛ ኃጢአተኞች ብንሆንም ይህ ፍቅር ከቶውንም አይቆምም። ፍቅር ለራሳችን ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ማሰላሰል ከቻልን፣ ሌሎችን እንደ ተወዳጅ ኃጢአተኞች የማየት ጸጋ ይሰጠናል። እራሳችንን በርህራሄ መረዳት ከቻልን በቤተሰባችን ውስጥ ያሉ ሌሎችን በርህራሄ መንገድ መረዳት እና መቀበል እንችላለን። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅር ታጋሽ፣ ቸር ነው፥ በደልን አይቆጥርም ያለው።

ለዚህ ጸጋ፣ ይቅር የሚለንን የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድንለማመድ በዚህ ወር ከቅዱስ አባታችን ጋር እንጸልይ። ያ ፍቅር በውስጣችን እንዲሰርጽ ስንፈቅድ፣ በቤተሰባችን ውስጥ ሌሎችን ይቅር እንድንል እንዲረዳን እግዚአብሔርን እንለምነው። እግዚአብሔር በእነሱ በኩል ወደ እኛ የሚያመጣውን ስጦታዎች እንድናገኝ ለስህተታቸው እና ውድቀታቸው የይቅርታ ልብ ሊኖረን እንደሚገባም መክረውናል።  
 

05 Mar 2025, 15:06