MAP

የጋና ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት የጋና ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት 

የጋና ብጹአን ጳጳሳት ተስፋ በክርስቶስ ድል ላይ የተመሰረተ መሆኑን በማረጋገጥ ለካቶሊኮች የዐቢይ ፆም መልዕክት አስተላለፉ

በጋና የሚገኙ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት በዚህ የዐቢይ ጾም ወቅት ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ እና ተስፋ እንደማያሳፍር ለክርስቲያኖች ባስተላለፉት መልዕክት ያረጋገጡ ሲሆን፥ እውነተኛ ተስፋ ክርስቶስ በኃጢአትና በሞት ላይ ባገኘው ድል ላይ የተመሠረተ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው፥ ምዕመናን ጸሎትን፣ መሥዋዕትነትና ፍቅርን በጸጋ እንዲቀበሉና ሁልጊዜም በእግዚአብሔር ምሕረት እንዲታመኑ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የጋና ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (GCBC) አባላት በያዝነው ዓመት እየተከበረ የሚገኘውን የተስፋ ኢዮቤልዩ ላይ በመመስረት የዐቢይ ፆምን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ተስፋ በክርስቶስ ድል ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለምዕመናን አረጋግጠው፥ በዚህ 40 ቀናትን በምንፆመው የዐቢይ ፆም ወቅት ምዕመናን ይህንን እንዲቀበሉ ጥሪ አድርገዋል።

ተስፋ ጊዜያዊ ስሜት አይደለም
ብጹአን ጳጳሳቱ አጽንዖት ሰጥተው እንደገለጹት እውነተኛ ተስፋ ጊዜያዊ በሆኑ ሁኔታዎች ላይ ሳይሆን በማይናወጥ የክርስቶስ ትንሣኤ መሠረት ላይ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም ለአማኞች መታደስ እና ብርታትን እንደሚሰጥ ገልጸው፥ “በዚህ የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት የትንሳኤው መልዕክት በላቀ ኃይል ያስተጋባል” ካሉ በኋላ ተስፋ ጊዜያዊ ስሜት ሳይሆን በክርስቶስ ድል ላይ የተመሠረተ ጽኑ ማረጋገጫ መሆኑን ያስታውሰናል ብለዋል።

በጋና ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ብጹእ አቡነ ማቲው ክዋሲ ጊያምፊ የተፈረመው መልእክት “የዐቢይ ጾም ምእመናን ይህንን በተስፋ እንዲቀበሉ፣ ሕይወታቸውን እንዲለውጡ እና ይህን ተስፋ ለሌሎች እንዲያካፍሉ ያዘጋጃቸዋል” በማለትም ይገልፃል።

ጋናዊያን ጳጳሳቱ “በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እና ፈተናዎች መካከል በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ዘላለማዊ ተስፋ ሁላችንንም ይሞላናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የእግዚአብሔር ፍቅር በመከራም ወቅት ይኖራል
የዐቢይ ጾም የእግዚአብሔር ፍቅር እና ምሕረት በመከራ ውስጥም እንደሚገኝ ክርስቲያኖችን የሚያስታውስ የተስፋ ወቅት እንደሆነ የጠቆመው የብጹአን ጳጳሳቱ መልዕክት፥ ወቅቱ በመስዋዕትነት እና በንሰሃ የሚገለጥ ሆኖ ሳለ፥ በመጨረሻ ግን በክርስቶስ ያለውን ተስፋ እንደሚያመለክት ገልጸው፥ ይህም የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመትን እንደሚያጠናክር እና አማኞች በእግዚአብሔር የመቤዠት ብሎም በአዲስ ህይወት ተስፋ እንዲታመኑ ያሳስባል።

ጳጳሳቱ በማከልም በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ካቶሊኮች ዐቢይ ጾምን ሲፆሙ የተገለሉትን በመደገፍ፣ በሐዘን ላይ ያሉትን በማጽናናት እና ብዙ ጊዜ በመለያየት እና በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር ሕያው ምስክሮች በመሆን በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ውስጥ ተስፋን እንዲያሳድጉ አበረታተዋል።

“ይህ የኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት ሁላችንም የዘላለም ሕይወት ተስፋን እንድናሰላስል ይጋብዘናል” ያሉት ብጹአን ጳጳሳቱ፥ ምክንያቱም ዐቢይ ጾም ምድራዊ ትግላችን ጊዜያዊ እንደሆነ እና የመጨረሻው ተስፋችን በመንግሥተ ሰማያት ተስፋ ላይ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህ አተያይ አማኞች በችግር ጊዜም ቢሆን በዓላማ፣ በድፍረት እና በደስታ እንዲኖሩ ያበረታታቸዋል በማለት በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

ዐቢይ ጾም፦ በጸጋ የተሞላ ወቅት
“የዘንድሮው ዐቢይ ጾም፥ በኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት ጸጋ የተሞላ ወቅት ነው” በማለት የገለጸው የብጹአን ጳጳሳቱ መልዕክት፥ ይህ ወቅት ክርስቲያኖችን እርሱን ለሚፈልጉ ሁሉ የሚበዛውን የእግዚአብሔርን ምሕረት እንደሚያስታውስ ይገልጻል።

“በጸሎት አማካኝነት ክርስቲያኖች በእርሱ መገኘት ተስፋን በማግኘት ወደ እግዚአብሔር ይቀርባሉ” ያለው መልዕክቱ፥ ጾም ራስን መግዛትን እንደሚያስተምር እና አማኞች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንደሚያስታውስ፥ ብሎም ምጽዋት ደግሞ የበለጠ ፍትሃዊ እና ሩህሩህ ዓለም የመገንባት ተስፋን ያሳያል በማለት ያብራራል።

ጳጳሳቱ “በዘንድሮው ኢዮቤልዩ ዓመት የምናሳልፈው የዐቢይ ጾም የጸሎትን ፍሬ እና ትሩፋት የምንለማመድበት፣ ጠንክረን የምንፆምበት እንዲሁም በክርስቲያን ማህበረሰቦች ውስጥ ምጽዋት የምናደርግበት ወቅት እንዲሆን ጸሎታችን ነው” ካሉ በኋላ በመጨረሻም፥ ይህ የዐቢይ ጾም ወቅት ምዕመናን በጣም አስቸጋሪ በሆኑ የሕይወት ጊዜያትም ጭምር በእግዚአብሔር መገኘት እንዲታመኑ ለማስታወስ የሚያገለግል መሆኑን በማሳሰብ፥ ክርስቲያን አማኞች በእምነት እና ሌሎችን በማገልገል ተስፋን የበለጠ ማስፋፋት እንዳለባቸው በመምከር አጠቃለዋል።
 

13 Mar 2025, 14:55