MAP

ስለ ሰላም መጸለይ ስለ ሰላም መጸለይ  (AFP or licensor)

የአውሮጳ ሃገራት ብጹአን ጳጳሳት በዐቢይ ጾም ወቅት ስለ ሰላም መጸለይ እንደሚገባ አሳሰቡ

የአውሮፓ ሃገራት ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ በዐቢይ ጾም ወቅት ፍትሐዊና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት እንደሚያደርጉ ገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የላቲን ሥርዓት ተከታይ የሆኑ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የዐቢይ ፆምን በሚጀምሩበት ዕለተ ረቡዕ አመድ በቅዱስ መስቀል ምልክት በግንባር የመቀባት ሥነ ስርዓት የሚካሄድ ሲሆን፥ በዚህ በዐቢይ ጾም ወቅት በአውሮፓ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ቁርባን ስግደት ስለ ሰላም እንደምትጸልይ ገልፃለች።

የአውሮፓ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት (CCEE) ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ ውጥኑ ሁሉንም የምክር ቤት አባላት እንደሚያካትት አብራርቷል።

ሰላም ለዩክሬን እና ለቅድስት ሀገር
እያንዳንዱ የጉባኤው አባል በዚህ የዐቢይ ፆም ወቅት “ለጦርነት ሰለባዎች፥ በተለይም በዩክሬን እና በቅድስት ምድር ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እና አምላክ የምህረት እጁን እንዲዘረጋ ለመጸለይ በማሰብ ቢያንስ በየዕለቱ አንድ መስዋዕተ ቅዳሴ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለው በመግለጽ ለዚህ የፆም ወራት የተዘጋጀውን ተነሳሽነቶች ገልጿል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የጤና ሁኔታ
የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤ መግለጫው አክሎም ተከታታይ ‘የቅዱስ ቁርባን ስግደት’ ዓላማው “የኅብረት ልምምድን ለማጎልበት እና ለመላው የአውሮፓ አህጉር ተጨባጭ የሆነ ተስፋን” ለማቅረብ እንደሆነ ገልጿል።

በዐቢይ ጾም ወቅት “ሁላችንም ወንድማማቾችና እህትማማቾች መሆናችንን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እና እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ ከእግዚአብሔር ምህረትን የምንለምንበት የጸሎት፣ የጾም እና የምጽዋት ጊዜ ነው” በማለት ያከለው መግለጫው፥ “በእነዚህ የስቃይ እና ህማማት ቀናት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጤና እንድንጸልይ ጥሪያችንን ደግመን እናቀርባለን” ብሏል።

የአውሮፓ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት (CCEE)
በአውሮፓዊያኑ 1971 ዓ.ም. በአውሮፓ የ13 የብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንቶች በመካከላቸው ህብረትን ለመፍጠር በመወሰን የአውሮፓ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤትን የመሠረቱ ሲሆን፥ ዛሬ ምክር ቤቱ በአውሮፓ አህጉር ውስጥ የሚገኙ 45 ሃገራትን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ 39 አባላትን ያቀፈ የጉባኤዎች ምክር ቤት እንደሆነ ይታወቃል።

ምክር ቤቱ ለአዲሱ የወንጌል ስርጭት ቁርጠኛ በመሆኑ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ለሚሳተፉ ሁሉም የቤተክርስቲያኑ መዋቅሮች ድጋፉን የሚሰጥ ሲሆን፥ በአውሮፓ የሚገኙ ሰዎችን እና ማህበረሰቦችን ለመድረስ በመላው አህጉሩ የወንጌልን እምነት እና እውነት ለመመስከር የታለሙ ጅምር ሥራዎችን ያበረታታል።

ከዚህም ባለፈ የአውሮፓ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ከሌሎች ዓለም አቀፍ እና አውሮፓውያን ተቋማት ጋር በመሆን በተለያዩ ማህበራዊ እና በቤተክርስትያን ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ በንቃት የሚሳተፍ ሲሆን፥ በክርስቲያናዊ አመለካከት መሰረት በእግዚአብሔር አምሳል እና ምስል የተፈጠረውን እያንዳንዱን ሰው ልጅ ክብር እና የሰብአዊ መብት መከበርን ለማበረታታት በንቃት እየሰራ እንደሆነም ተገልጿል።
 

06 Mar 2025, 14:07