የአውሮፓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፥ የአውሮፓ ኅብረት የተስፋ ብርሃን ሆኖ እንዲያገለግል አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአውሮፓ ኅብረት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፥ አውሮፓን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተከሰተ ያለው አደገኛ የግጭት አዙሪት አሳሳቢነት እየጨመረ ባለበት ወቅት፥ የአውሮፓ ኅብረት መሠረት የሆነውን የሰላም፣ የሕግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ መብት መከበር እና የዴሞክራሲ መርሆዎችን በአውሮፓ እና በውጪ አገራት ውስጥ እንዲያከብር ተማጽነዋል።
የአውሮፓ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ይህን ተማጽኖአቸውን ያቀረቡት የአውሮፓ ኅብረት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን ከመጋቢት 17-19/2017 ዓ. ም. ድረስ በሮም አቅራቢያ ኔሚ ከተማ ባካሄዱት ጉባኤ ማጠቃለያ ሲሆን፥ ጳጳሳቱ በወቅታዊው የዓለም ሁኔታ ላይ በመወያየት፥ አውሮፓ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ወዲህ ከገጠሟት አስከፊ ቀውሶች መካከል በአንዱ ውስጥ እንደምትገኝ ለቫቲካን፣ ለአውሮፓ ኅብረት እና ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች ለመጡት የምሁራን ተወካዮች ገልጸዋል።
እያንሰራራ ባለው ብሔራዊነት ውስጥ የባለብዙ ጎን ወገናዊነት ቀውስ
ብጹዓን ጳጳሳቱ በጉባኤያቸው መጨረሻ፥ “አውሮፓን በተስፋ መመልከት” በሚል ርዕሥ ባወጡት መግለጫቸው፣ በብሔራዊነት መንሰራራት ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የዓለም አቀፍ ግንኙነት መፈራረስ፣ የዴሞክራሲያዊ መርሆች መዳከም፣ መገለል እና የባለብዙ ወገን ትብብር ማሽቆልቆል ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በእነዚህ ቀውሶች ምክንያት የሚታዩ ፉክክሮች እና ግጭቶች ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥሱ መሆናቸውን የገለጹት ጳጳሳቱ፥ የዩክሬይ ሕዝብ ስቃይ የሰላምን መዳከም እና አዲስ ዓለም አቀፍ ትብብር ስለማስፈለጉ ትልቅ ማስረጃ ሆኖ እንደሚያገለግል አስረድተዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በተመሠረተበት መርህ እና ሃሳብ ላይ መቆም
በእነዚህ ችግሮች መካከል የአውሮፓ መሪዎች ካለፉት ታሪካዊ ክንውኖች ውስጥ ሃሳብ እንዲወስዱ ያሳሰቡት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍርሃት በኋላ ለአውሮፓ ማኅበረሰብ መሠረት የጣለውን የሹማን መግለጫን እና እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1975 ዓ. ም. የጸደቀውን የሄልሲንኪ የመጨረሻ ሕግን አስታውሰዋል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ በተጨማሪም እነዚያ ያለፉት ጊዜያት ውይይት፣ ትብብር፣ ሰብዓዊ ክብር፣ አብሮነት፣ ዴሞክራሲ እና የጋራ ተጠቃሚነት ለመሳሰሉት የጋራ እሴቶች ቁርጠኝነት፣ ለሰላም እና መረጋጋት መሠረት ሆነው እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል። ዓለም አውሮፓን ለመሪነት በሚፈልግበት በዚህ ወቅት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አህጉሪቱን የሰላም ተስፋ እና የልማት ምንጭ አድርገው እንደሚመለከቷትም ታውቋል።
ቁጥጥር ያልተደረገበት ወታደራዊ የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም አውሮፓ አደጋ ላይ ይጥላታል
በጳጳሳቱ መግለጫ ላይ ከተነሱት ቁልፍ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሩሲያ በዩክሬይን ላይ ያደረገችው ሙሉ ወረራ እንደሆነ ተመልክቷል። በአውሮፓ ኅብረት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ በሚደረገው ውይይት ውስጥ ወሳኝ ርዕሠ ጉዳይ የሆነው የአውሮፓ የመከላከያ ኃይል የሚመለከት ሲሆን፥ አሁን ደግሞ አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ከአውሮፓ መራቁ ከውይይት ርዕሦች መካከል አንዱ እንደነበርም ተመልክቷል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ አውሮፓ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል እንደሚያስፈልጋት ቢገነዘቡም፣ ቁጥጥር ያልተደረገበት ወታደራዊ የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም ከሰላም ይልቅ ለንግድ ዓላማ መቆሙ አውሮፓን አደጋ ላይ እንደሚጥላት እና ይህም ወሳኝ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ሰብዓዊ እና አካባቢያዊ ዋጋን ሊያስከፍል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የሰላም ውጥን እና የእድገት ምንጭ ሆኖ መቀጠል አለበት
ተጨማሪ ግጭቶችን ለመከላከል እና የአውሮፓ የመጀመሪያ ተልዕኮ የሆነው የሰላም ውጥን ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ዘዴዎችን የደገፉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ የአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፋዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደረጃውን ለማጠናከር የሚያደርውን ጥረት ቢገነዘቡም ነገር ግን መሰል ጥረቶች የኅብረቱን ታሪካዊ ቁርጠኝነት ዋጋ ሊያስከፍል እንደማይገባ አጥብቀው ተናግረዋል።
“አውሮፓ በድንበሯ ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉትን ድሃ አካባቢዎችን፣ ግጭቶችን እና ድህነትን የሚሸሹ ስደተኞችን እና በፍትህ መጓደል የሚሰቃዩ ተጋላጭ ወገኖችን መደገፍ መቀጠል አለባት” ሲሉ አሳስበዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አክባሪ ዋና ተጠቃሽ ሆኖ ቀጥሏል
መግለጫው፥ የአውሮፓ ኅብረት እንደ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን፣ ተዓማኒነትን፣ ማኅበራዊ ፍትህን እና ዘላቂነት ያለው የአካባቢ ጥበቃን ሊጎዳ የሚችል የፖሊሲ ለውጥ ሊኖር እንደማይገባ አስጠንቅቋል።
የአውሮፓ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በመግለጫቸው ማጠቃለያ፥ አውሮፓ በመሠረታዊ መርሆቹ ላይ ሆኖ አንድነቱን እንዲቀጥል እና ለሕዝቦቹ ብቻ ሳይሆን ለሰፊው የዓለም ማኅበረሰብም የተረጋጋ ኃይል እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
“የአውሮፓ ኅብረት በዛሬዎቹ አስተማማኝ ባልሆኑ ወቅቶች ለመሠረታዊ መርሆቹ ታማኝ ሆኖ እንደሚቀጥል፣ ለአካባቢው አገራት እና ለዓለም አንድነት ጭምር እምነት የሚጣልበት የተባበረ ኃይል ሆኖ እንደሚቀጥል ተስፋችን ነው” ሲሉ መግለጫቸውን ደምድመዋል።