MAP

አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ  (AMBER BRACKEN)

በካናዳ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት አዲስ የወጣው የግብር ህግ እንደሚያሳስባቸው ገለጹ

በካናዳ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በካናዳ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያሳድሩትን ከቀረጥ ነፃ ግብር ሁኔታ እና እምነትን መሰረት ያደረጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ፍቃድ እንዲሰረዝ የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሁለት ምክረ ሃሳቦች ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የሊበራል ፓርቲ መሪ ሆነው ከተመረጡ በኋላ አርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በይፋ ሥራ የጀመሩ ሲሆን፥ ቀደም ሲል የካናዳ እና የዩናይትድ ኪንግደም ማዕከላዊ ባንኮችን ይመሩ የነበሩት ካርኒ ወደ ስልጣን የመጡት የቀድሞ የባንክ ባለሙያ እና ለአስር ዓመታት ያህል በስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ስራቸውን መልቀቃቸውን ያስታወቁትን ጀስቲን ትሩዶን በመተካት እንደሆነ ይታወቃል።

ቀጣዩ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ አለመረጋጋት የገጠማትን አገር ሲረከቡ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር አገራቸው የገባችውን የንግድ ጦርነት ለማሸነፍ ቃል የገቡ ሲሆን፥ የ59 ዓመቱ ካርኒ ድላቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ካናዳ ላይ ታሪፍ የጣሉትን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመወረፍ “አሜሪካ ስህተት ልትሰራ አይገባም” ብለዋል።

ማርክ ካርኒ መንግሥታቸው አሜሪካ ክብር እስክታሳያቸው ድረስ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የተጣለው ታሪፍ እንደሚፀና የተናገሩ ሲሆን፥ የካናዳ ኢኮኖሚ ከአሜሪካ ጋር ባለው ትልቅ የንግድ ልውውጥ ላይ እንደተመሰረተ እና በትራምፕ የሚጣለው ታሪፍ ሙሉ ለሙሉ ገቢራዊ ከሆነ ኢኮኖሚው የውድቀት ስጋት ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል።

አዲሱ የካናዳ መንግስት የመጀመሪያ ሥራ ትልቅ ፈተና የሆነውን አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ መሪ ዶናልድ ትራምፕ ከካናዳ ጋር የጀመሩትን የንግድ ጦርነት መፍታት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ካናዳን 51ኛው የአሜሪካ ግዛት አድርገው ለመጠቅለል ያሳዩት ፍላጎት እና ዛቻ በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል ታይቶ የማያውቅ ቀውስ አስከትሏል።

ባለፈው ወር አሜሪካ በካናዳ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደጣለች እና ካናዳም ለእርምጃው ምላሽ በመስጠት በአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ የጣለች ሲሆን፥ የአሜሪካ እርምጃ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመጣል የተወሰደ ነው የሚል ክስ ቀርቦበታል።

የታቀዱት ለውጦች
ከእነዚህ ማስፈራሪያዎች እና ቅስቀሳዎች በስተጀርባ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ፍጹም የተለየ ተፈጥሮ ያለው ሌላ ጉዳይ የተከሰተ ሲሆን፥ በዚህም ገዢው የሊበራል መንግስት ካናዳ ውስጥ የሚገኙ ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን የበጎ አድራጎት ፍቃድ ለመሻር ማቀዱ ተነግሯል። የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ታህሳስ ወር ላይ 462 የውሳኔ ምክረ ሃሳቦችን ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ሁለት አንቀጾች ይህንን ጉዳይ በቀጥታ እንደሚመለከቱ መረጃዎች ያሳያሉ።

እነዚህ ሁለቱ አንቀፆች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የፀረ-ውርጃ አንቀጽ ለመሻር ሃሳብ የሚያቀርበው አንቀጽ 429 እና ይህንን ፖሊሲ ለሁሉም የሃይማኖት ድርጅቶች እንዲተገበሩ ምክረ ሃሳብ የሚያቀርበው አንቀጽ 430 ሲሆኑ፥ አንቀጽ 430 እነዚህ ድርጅቶች የበጎ አድራጎት ደረጃን እንዳያገኙ ለመከላከል ያለመ ሲሆን፥ ይህ ደግሞ ‘በካናዳ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል’ ሲል በኪውቤክ የሚገኘው እና ‘ሌ ቨርቤ’ ተብሎ የሚታወቀው የካቶሊክ ሚዲያ አዘጋጅ ቤንጃሚን ቦይቪን ለቫቲካን ዜና አስረድቷል።

አብያተ ክርስቲያናት የማንቂያ ደውሉን ማሰማታቸው
በካናዳ ውስጥ የሚገኙ ቤተክርስቲያኖችን፣ መስጊዶችን እና ምኩራቦችን ባካተተው የሃይማኖት ተቋማት የሚከናወኑ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ማኅበራትን የሚያሳትፍ ሲሆን፥ “እስካሁን ድረስ በካናዳ ማህበረሰብ ውስጥ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ለማበረታታት በግለሰቦች ለሚደረገው ልገሳ መንግስት የተወሰነውን ከፍሏል” ሲል ቤንጃሚን ስለ ሁኔታው ተናግሯል።

የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የቶሮንቶ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፍራንክ ሊዮም ለገንዘብ ሚኒስትሩ ዶሚኒክ ሌብላንክ በፃፉት ደብዳቤ፥ ሀይማኖታዊ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሁሉንም ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረቶች እና የተቸገሩትን ለመንከባከብ ያለመታከት በሚሰጡት አገልግሎት የሀገሪቷን መዋቅሮች እንደሚያጠናክሩ በመግለጽ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አሁን በወጣው ህግ ላይ ያላትን ስጋት ገልጸው፥ ሃሳቡን “ፍፁም አሳፋሪ እና ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ያወገዙ ሲሆን፥ በጎ አድራጊ ተቋማት እና የሀይማኖት ድርጅቶች የበጎ አድራጎት ደረጃቸውን ካጡ፥ በካናዳ ለረጅም ጊዜያት የእምነት፣ የአምልኮ እና የሃይማኖት ተቋማት በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን የማይተካ ሚና እውቅና ማሳጣት ይሆናል በማለት ገልጸዋል።

በጀቱ እንዲሁም አንቀፅ 429 እና 430 እስካሁን ተቀባይነት ያላገኙ ቢሆንም፣ በመላ ሀገሪቱ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት በምክረ ሃሳቦቹ ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን፥ የካናዳ ኢቫንጀሊካል ፌሎውሺፕ ለገንዘብ ሚኒስትር ዶሚኒክ ሌብላንክ በላከው ግልጽ ደብዳቤ ላይ “የሃይማኖት ማህበረሰቦች መኖር እና በሚሰጡት አገልግሎት ከራሳቸው አባላት አልፈው ለካናዳ ማህበረሰብ ይጠቅማሉ” ብለዋል።

በካናዳ ማህበረሰብ ላይ የደረሰ ጉዳት
በእርግጥ፣ በመላው ካናዳ ያሉ የሃይማኖት ማህበራት የበጎ አድራጎት ተፅእኖ (የካናዳ ገቢዎች ኤጀንሲ እንደገለጸው በአገሪቱ ካሉት 73,000 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ በግምት 40 በመቶ ያህሉ) ከሃይማኖት ሚና ባሻገር በርካታ ሥራ እየሰሩ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ ባለፈው ታኅሣሥ በካርዱስ የምርምር ማዕከል የታተመ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ለአብያተ ክርስቲያናት እና ሃይማኖት ድርጅቶች ከቀረጥ ነፃ መውጣት መንግሥትን ጨምሮ ለሁሉም ካናዳዊያን ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው የጠቆመ ሲሆን፥ ጥናቱ እንደሚያመለክተው የሀይማኖት ተቋማት ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚያበረክቱት መዋጮ ከተፈቀደላቸው ከቀረጥ ነፃ ዋጋ 10.5 እጥፍ እንደሚበልጥ ዘግቧል።
 

17 Mar 2025, 12:43