የተለያዩ ክርስቲያኖች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጤና እንዲሁም በህመም ለሚሰቃዩ ሁሉ በአንድነት ጸለዩ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጤና እንዲሁም በህመም እየተሰቃዩ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ሁሉ የተደረገው እና “ሕያው እግዚአብሔር ሆይ፣ ከተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር ወደ ፊትህ መጥተን ለታመሙት እና ስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዲሁም በዚህ ወቅት ታመው ስቃይ ውስጥ ለሚገኙት አገልጋይህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጤና ትሰጥ ዘንድ እንለምንሃለን” በማለት የሚጀምረው የጸሎት ሥነ ሥርዓት የተካሄደው መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ዓርብ ከሰዓት በኋላ ፒሳይበስ በሚገኘው እና የዓለም አቀፍ ወጣቶች ማዕከልም ጭምር ሆኖ በሚያገለግለው የቅዱስ ሎሬንዞ የሮማውያን ደብር ውስጥ ነው።
የታመሙትን እና ተንከባካቢዎችን ማስታወስ
የክርስቲያን አንድነትን በሚያበረታታው በታይዜ ማህበረሰብ ገዳም ጽህፈት ቤት እና የሮም ክርስቲያናዊ የውይይት መድረክ ጽህፈት ቤት ከአንግሊካን ማዕከል እና ከሮማው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ እና የተሐድሶ አብያተ ክርስቲያናት ቢሮዎች ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የጸሎት መርሃ ግብር ላይ “ነፍሴ ሆይ ጌታን ባርኪ” የሚለው የመዝሙረ ዳዊት ክፍል ከተነበበ በኋላ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ኤፌሶን ሰዎች (6፡13-18) በጣሊያን፣በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛ፣ በስፓኒሽ እና በፈረንሳይኛ ተነቧል።
ከዚህም በተጨማሪ የምዕመናን ጸሎት በቤተክርስቲያኑ ተወካዮች እና ከተወሰኑ ወጣቶች መሪነት በተለያዩ ቋንቋዎችም የተደረጉ ሲሆን፥ በተለይም ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “በህመማቸው ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ብርታትና ሰላም” መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣቸው እንዲሁም “ለታመሙት ሁሉ፣ ህሙማኑን ለሚረዱ እና ለሁሉም የህክምና ባለሙያዎች ጸሎት ቀርቧል።
ስለ ሰላም የተደረጉ ጸሎቶች
በመርሃ ግብሩ ላይ በተለይ “ለዩክሬን፣ ለጋዛ፣ ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ለሄይቲ፣ ለኒካራጓ እና በችግር በተሞላው ዓለማችን እንዲሁም ጦርነት ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ” ሰላም እንዲነግስ የሰላም ጸሎት የተደረገ ሲሆን፥ የሰው ልጅ “ከአምላክ የተሰጠን ስጦታ የሆነውን ፍጥረትን የመንከባከብ” ኃላፊነት ይበልጥ እንዲገነዘብ ተስፋ በማድረግ በዓለም ሙቀት መጨመር እና በምድር ሀብት ብዝበዛ ለተጎዱ ሰዎች ጸሎት ቀርቧል። የመጨረሻው የጸሎት መነሻ ሃሳብም ለክርስቲያኖች አንድነት ተደርጓል።
የክርስቲያናዊ ህብረት በረከት
ከተለያዩ የክርስቲያን ማህበረሰብ ተወካዮች በጋራ የተሰጠው የመጨረሻው የቡራኬ መርሃ ግብር ከመካሄዱ በፊት እግዚያብሄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ከህመማቸው እንዲፈውሳቸው ጸሎት በድጋሚ የቀረበ ሲሆን፥ በመጨረሻም ሥነ ስርዓቱ የታይዜ ገዳም ሃላፊ ወንድም ማቲው፣ ሊቀ ጳጳስ ፍላቪዮ ፔስ የክርስቲያን አንድነትን ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ታራ ኩርሌቪስ ከተሐድሶ አብያተ ክርስቲያናት፣ ማቲው ኤ ላፈርቲ ከሜቶዲስት፣ የአርሜኒያ ሐዋርያዊ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ኻጃግ ባርሳሚያን እና ጂም ሊንቲከም የአንግሊካን ቤተክርስቲያናት ህብረት በጋራ በመሆን “በጌታ መታመን መልካም ነው” የሚል ዝማሬን በማቅረብ ተጠናቋል።