MAP

ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በሮም የዊቨርስ ኦፍ ሆፕ ሽልማትን ሲያስጀምር ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በሮም የዊቨርስ ኦፍ ሆፕ ሽልማትን ሲያስጀምር 

“የተስፋ ምንጮች” ወይም 'ዊቨርስ ኦፍ ሆፕ' ሽልማት ሴቶችን ለማብቃት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ተባለ

ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በካቶሊክ ድርጅቶች በኩል ሴቶች በቤተሰቦቻቸው፣ በማህበረሰባቸው እና በህብረተሰባቸው ውስጥ የተስፋ ምንጮች እንዲሆኑ ለማገዝ “ዊቨርስ ኦፍ ሆፕ” (Weavers of Hope) የተባለ ሽልማት ይፋ ማድረጉ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በየዓመቱ በአውሮፓዊያኑ ማርች 8 ላይ በሚከበረው የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓል ላይ ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ወይም ዓለም አቀፉ ካሪታስ በመሠረታዊነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለመለወጥ የሚያግዝ “ዊቨርስ ኦፍ ሆፕ” የተባለ ሽልማትን ማስጀመሩ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም ትልቅ የድጋፍ ተነሳሽነት ነው ተብሏል።

ለተስፋ ፈጣሪዎች የሚሰጥ ሽልማት                                                                                                                                                                                                      ለአደጋ የተጋለጡ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን የሚያበረታቱ ለሁሉም ድርጅቶች እና ፕሮጀክቶች ክፍት የሆነው የዊቨርስ ኦፍ ሆፕ ሽልማት በከፊል የተነሳሽነቱ ያገኘው በኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ በካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ከፍተኛ ኦፊሰር የሆኑት ስቴፋኒ ማጊሊቪሬይ ስለ ሽልማቱ እንዳብራሩት ግቡ “ሴቶች በዓለም ዙሪያ በቤተሰብ፣ በማህበረሰቦች እና በህብረተሰብ ውስጥ እንዴት ተስፋ እንደሚገነቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው” ብለዋል። 

በብዙ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ሴቶች የትምህርት እና የተለያዩ የሥራ እድሎች የተገደበ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ለአቅመ ሄዋን ሳይደርሱ በግዳጅ ወደ ትዳር እንደሚገቡ እና እነዚህን ሴቶቹ የሚያጋጥሟቸውን ቀጣይ የሆኑ እንቅፋቶች ከመቅረፍ አንፃር ሴቶችን ለማብቃት በሚደረገው ጥረት ላይ ኢንቨስት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ወይዘሮ ስቴፋኒ በአጽንዖት ከጠቆሙ በኋላ፥ “ምክንያቱም ያለ ግብዓት ምንም ዓይነት እድገት ማምጣት አይቻልም” ብለዋል።

የዊቨርስ ኦፍ ሆፕ ሽልማት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር፣ ብሎም በመካሄድ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል ጭምር እንደሚረዳ የተገለጸ ሲሆን፥ ሴቶችን ለማብቃት በሚደረገው ጥረት ወቅት በተሰጡት ምስክርነቶች እና መልካም ልምዶች ላይ በማተኮር ‘እኩልነት፣ መገናኘት፣ መታደስ’ በሚል ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ባለፈው ዓመት ያሳተመውን መመሪያ መጽሃፍ እንደሚከተል ተገልጿል። በመሆኑም ይህ ሽልማት ከግብአትነት እና ከንድፈ ሃሳባዊ አካሄድ በመሰረታዊ ደረጃ ወደ ትግበራ የምንሄድበት መንገድ ይሆናልም ተብሏል።

አዲስ ነገር ሳይሆን ነባሩ የሚከበርበት ነው
ሽልማቱ ቀደም ሲል በዓለም ዙሪያ እየተከናወኑ ላሉት ጅምሮች እውቅና የሚሰጥበት መንገድ ሲሆን፥ በዚህም አካሄድ አራት ድርጅቶች ወይም ፕሮጀክቶች በጎረጎሳዊያኑ 2025 መገባደጃ ላይ የአንድ ዓመት ስጦታ ይሸለማሉ።

የአንድ ዓመት የእርዳታ እቅድ ብቻ ቢሆንም፥ አንዳንዴ ወደ ተሻለ ቦታ የሚያደርስ ትንሽ የገንዘብ ወይም የግብአት ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ወይዘሮ ስቴፋኒ ገልጸዋል።

ይህ ተልዕኮ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ያስረዱት ስቴፋኒ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎች፣ ቡድኖች እና ድርጅቶች ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማሳየት እና ለማበረታታት ብሎም ተስፋን ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ነገር ግን ይህ ተልዕኮ ሊሳካ የሚችለው ትብብር ሲኖር ብቻ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው ከገለጹ በኋላ፥ “ለሴቶች ለውጥ የምናመጣው እንደ እኛ ተመሳሳይ ስራዎችን የሚሰሩ እና የጋራ ዓላማ ያላቸውን ሌሎች ድርጅቶችን በመደገፍ ብቻ ነው” ብለዋል።
 

13 Mar 2025, 12:34