ብፁዕ ካርዲናል ማኬልሮይ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለሰላም ያቀረቡትን ጥሪ በማስታወስ ፈውስ እንዲያገኙ እንደሚጸልዩላቸው ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዋሽንግተን ዲሲ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አዲስ የተሾሙት ብፁዕ ካርዲናል ሮበርት ማኬልሮይ ያገለግሉበት የነበረውን በዩናይትድ ስቴትስ የሳንዲያጎ ሃገረ ስብከትን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ባደረጉት የመጨረሻው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከህመማቸው አገግመው እንዲወጡ ጸሎት እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል።
ለዋሽንግተን ሃገረስብከት ስምንተኛ ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሾሙት ብጹእ ካርዲናል ማኬልሮይ የመጀመሪያውን መስዋዕተ ቅዳሴ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ለዓለም ሰላም ጸሎቶች
በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ከጋዜጠኞች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው ብፁዕ ካርዲናሉ፥ በመጀመሪያ ደረጃ ሀገረ ስብከቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከህመማቸው እንዲያገግሙ ለጸሎት እንዲተባበር ካስታወሱ በኋላ፥ ባለፈው ሳምንት የሳንዲያጎ ሀገረ ስብከት ካህናት በሙሉ በዓለም ዙሪያ ካሉ ሰዎች ጋር በመንፈሳዊ አንድነት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጤና በልዩ የጸሎት አገልግሎት መሰባሰባቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በግጭት፣ በጦርነት እና በረሃብ ምክንያት ለሚሰቃዩ በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰዎች ዘወትር እንደሚጸልዩ ያስታወሱት ካርዲናሉ፥ እኛም በምላሹ ብጹእነታቸው ታመው ስቃይ ውስጥ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት “አምላክ በመከራቸው ወቅት እንዲረዳቸው፣ ሰላሙን እንዲሰጣቸው፣ ብሎም ብርታትን እና ፈውስን እንዲሰጣቸው” ጠንክረን ልንጸልይላቸው ይገባል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ላሳዩት ሃዋሪያዊ ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ብጹዕ ካርዲናል ማኬልሮይ፥ የቤተክርስቲያኗን አገልግሎት ለሁሉም በተለይም ለድሆች፣ ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች እና ለተገለሉት ሁሉ ለማዳረስ እና ለማስፋፋት ብጹእነታቸው ላደረጉት ጥረቶች ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፥ በርካታ ብጥብጥ እና ግጭት ባለበት ዓለም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የፍቅር፣ የርኅራኄ እና የመተሳሰብ ምልክት የሆነውን የወንጌል መልዕክት ለዓለም ማካፈላቸውን እንዲቀጥሉም ጥሪ አድርገውላቸዋል።
ምስጋና ለሳን ዲያጎ
ብፁዕ ካርዲናል ማኬልሮይ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ለአሥር ዓመታት ያክል ያገለገሉበትን የሳንዲያጎ ሀገረ ስብከት ሲሰናበቱ የተሰማቸውን ልባዊ ስሜት በመግለጽ፥ በነበራቸው የአገልግሎት ዘመን ሃገረ ስብከቱን እና ያቀፈውን ጠንካራ ማህበረሰብ በደስታ በማስታወስ፥ የባህል ስብጥር ያለበት፣ ታላቅ ብዝሃነት እና ንቃተ ህሊና ያለው ሁሌም የሚናፍቁት ቤተሰብ እንደሆኑ አስታውሰዋል።
የስደተኞችን ክብር መጠበቅ
ብፁዕ ካርዲናል ማኬልሮይ በሮም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ስላደረጉት ስብሰባ ተጠይቀው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዩናይትድ ስቴትስ እና በሜክሲኮ መካከል ባለው ድንበር አካባቢ ስላለው ሁኔታ፣ በተለይም ከክስተቱ ከባድነት አንፃር ፍልሰተኞች እንዴት እንደሚስተናገዱ በተደጋጋሚ እንደሚጠይቋቸው ጠቁመው፥ በውይይቱ ወቅት ሀገረ ስብከታቸው ውስጥ የሚገኙ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ለስደተኞች እና ፍልሰተኞች የሚያደርጉትን ሰብአዊ አገልግሎቶችን ለብጹእነታቸው ማስረዳታቸውን ካስታወሱ በኋላ፥ በአንድ ወቅት በቀን ወደ ስምንት መቶ ለሚጠጉ የጥገኝነት ወይም የስደተኛ ሁኔታ ጥያቄን በተመለከተ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን እስኪያይ ድረስ በህጋዊ እና በጊዜያዊነት ወደ ሀገር ለገቡ ሰዎች የጤና እና መሠረታዊ ፍላጎቶችን እንዴት እንደረዱ ጭምር ለብጹእነታቸው መንገራቸውን ገልጸዋል።
የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የአሜሪካ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ በአሜሪካ አስተዳደር ላይ ስለመሰረተው ክስ የተጠየቁት ብጹእ ካርዲናሉ፥ ዋናው ምክንያት መንግስት ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ለተዋዋላቸው እና ለሚሰጡት አገልግሎቶች በድንገት ክፍያን በማቆሙ ምክንያት ክስ እንደተመሰረተ አስታውሰዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ማኬልሮይ በዚህ ጉዳይ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቅርቡ ለአሜሪካ ብጹአን ጳጳሳት የጻፉትን ደብዳቤ አስታውሰው፥ ብጹእነታቸው በመልዕክታቸው አሜሪካ እንደ ሀገር በስደተኛ እና በፍልሰተኛ ፍሰቶች ድንበሯን በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ከሁሉም በፊት ለሰው ልጅ ክብር ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ካርዲናሉ ስደተኞችን ህጋዊ መረጃ ያልያዙ ህገወጥ በማለት በመፈረጅ ወይም ሁሉንም እንደ ወንጀለኞች በመፈረጅ እየተካሄደ ባለው “ሰፋ ያለ የባህል ጥቃት” ላይ ያላቸውን ስጋት አጋርተዋል።
ማኬልሮይ ሃገራቸው ላይ ያለውን ግጭትን፣ ጥቃትን ወይም አስከፊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ሸሽተው ወደ ሀገራቸው የገቡትን ህጋዊ ደረጃ ያላቸውን በርካታ ሰዎችን በማስታወስ፥ ሁሉንም እንደወንጀለኛ መፈረጅ ተገቢ እንዳልሆነ በሰጡት አጠቃላይ መግለጫ አስጠንቅቀዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መጀመሪያ ላይ ማስታወስ የሚገባን ነገር እንደሆነ እና ሁል ጊዜም የሰውን ክብር ማስቀደም እንደሚገባን ያስታውሱናል ያሉት ካርዲናሉ፥ “ከፊታችን ካሉት የጋራ ፈተናዎች ጋር የምንታገል ሁላችንም ወንድሞች እና እህቶች መሆናችንን” እንድናስታውስ እያሳሰቡን ነበር ብለዋል። ካርዲናሉ አክለውም “በኢሚግሬሽን የሚከሰቱ እውነተኛ ችግሮች ምን እንደሆኑ እና ድንበር ማስጠበቅን ጨምሮ እንዴት እንደምናስተናግድ ማየት አለብን፥ ነገር ግን ሰዎችን እንደ ወንጀለኛ በመቁጠር ሰብአዊነትን ማሳጣት ዬለብንም” ብለዋል።
ወንጌልን መመስከር
ብፁዕ ካርዲናል ማኬልሮይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዛሬው ኅብረተሰብ ውስጥ ያላትን ሚና በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሚና “የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት ወይም የፖሊሲ ችግሮችን መፍታት ሳይሆን፥ እንደ ቤተ ክርስቲያን ስለ እምነታችን መመስከር ያለብን ቤተ ክርስቲያኒቷ በሕዝብ ሥርዓት ውስጥ የተለየ የፖለቲካ ሚና ስለሌላት፥ ይልቁንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና ከካቶሊክ አስተምህሮ አንፃር በኅብረተሰቡ ውስጥ በሚሰጡ መመሪያዎች ላይ አስተያየት የመስጠት የሞራል ሚና አላት ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ እና በእርግጥም መላው ዓለም ዛሬ ላይ እያጋጠማቸው ያለውን ተግዳሮት በማንሳት “በማህበረሰባችን ውስጥ ሩህሩህ ማህበረሰብ ማለት ምን ማለት ነው? በእያንዳንዱ ሰው እኩል ክብር እናምናለን ማለት ምን ማለት ነው? ይሄንንስ እንዴት ነው የምንኖረው? የሚለውን መመለስ አለብን” ያሉት ካርዲናሉ እነዚህ የምሥክር ቦታዎች ናቸው ብዬ የማስበው በአሁኑ ወቅት በምናደርጋቸው ውይይቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ቤተክርስቲያን ወደፊት እንድትመጣ የተጠራችበት ነው…፣ ምክንያቱም በአገራችን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነን” ብለዋል።
ብጹእ ካርዲናል ማኬልሮይ በመጨረሻም ቤተክርስቲያን የሰውን ልጅ ክብር ከማክበር አንፃር ለመመስከር የምትፈልገው በሚደረጉት ውይይቶች እና በሚወጡት ፖሊሲዎች ላይ የወንጌል እሴቶች መተግበር አለመተግበሩን ማረጋገጥ ነው” በማለት አጠቃለዋል።