MAP

በዚምባብዌ፣ ሐራሬ በሚገኘው ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች በዚምባብዌ፣ ሐራሬ በሚገኘው ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች  (ANSA)

የዚምባብዌ ቤተክርስቲያን የሰው ልጅ ቅድስና ለማስጠበቅ የመንግስት አጋርነትን መጠየቋ ተነገረ

የዚምባብዌ ካቶሊክ ቤተክርስትያን የሰው ልጅ ህይወትን የሚያከብር እና ለአደጋ የተጋለጡትን የሚጠብቅ ማህበረሰብ ለመገንባት የሰውን ክብር፣ ፍትህ እና የሞራል እሴቶችን ለማጠናከር እና ለማሳደግ ከመንግስት ጋር ተባብሮ መስራት እንደሚገባ አሳስባለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኢመርሰን ምናንጋዋ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. የሞት ቅጣት መሰረዙን ተከትሎ የዚምባብዌ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የፍትህ እና የሰላም ኮሚሽን (CCJPZ) መንግሥት በኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት መንፈስ ሰብዓዊ ክብርን፣ ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን እና ማኅበራዊ ፍትህን በማስፋፋት ረገድ ከቤተክርስቲያን ጋር እንዲተባበር ጠይቋል።

በዚምባብዌ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የፍትህ እና የሰላም ኮሚሽን እና በካቶሊካዊ የፓርላማ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ሊቀ መንበር በሆኑት የገዌሩ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሩዶልፍ ኒያንዶሮ የተፈረመው ሃዋሪያዊ መልዕክት እንደሚገልጸው እያንዳንዱ ግለሰብ የሚከበርበትና የሚጠበቅበት ፍትሐዊና ሩህሩህ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሃይማኖት ተቋማትና በመንግሥት መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቀ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው የመልዕክታቸውን መሠረት ያደረጉት የኢዮቤልዩ ዓመት ‘የተስፋ ነጋዲያን’ በሚል መሪ ቃል ላይ እንደሆነ እና ዓመቱም በኃጢአት ሥርየት እና በተለይም በትጋት በመመላለስ ባሕርይ ያለው ሁላችንም የምንናፍቀው የእግዚአብሔር ምህረት ሙሉ መገለጫ ነው ብለዋል።

“ይህም በመሆኑ የተሰጠንን የተስፋ ጭላንጭል የምናበራበት ጊዜ ነው” ያሉት ጳጳሱ፥ ወደፊትም ክፍት በሆነ መንፈስ፣ በፍቅር ልብ እና በምሕረት እይታ እያንዳንዱ ሰው አዲስ ጥንካሬ እና እርግጠኝነት እንዲያገኝ መርዳት ይገባል ብለዋል።

ስህተትን አውግዝ፣ የግለሰቦችን ክብር ግን ጠብቅ
ብጹእ አቡነ ኒያንዶሮ እንዳሉት በዚህ የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት በሥጋም ሆነ በመንፈሳዊ ዓለም የእምነትን ውበት እንደገና የምናገኝበት እና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የመሆንን ቃል ኪዳን የምናድስበት ነው ካሉ በኋላ፥ ለተጎጂ ቤተሰቦች የድጋፍ እና የምክር አገልግሎት ለመስጠት ቤተክርስቲያን እና መንግስት በጋራ እንዲሰሩ በማሳሰብ፥ “ይህ ኃጢያትን መጥላት እንዳለብን ነገር ግን ኃጢአተኛውን መጥላት እንደሌለብን ከሚገልጸው የእምነት አስተምህሮ ጋር የሚስማማ ነው” በማለት አክለዋል።

በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የሁሉንም ሰው ክብር እንዲያከብሩ፣ የሕግ አውጭው አካል የቅጣት አወሳሰን ሕጎች ፍትሐዊ ሆነው እንዲቀጥሉ እና ከወንጌል እሴቶች ዘላቂነት ባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎችን እንዲያሟሉ በማድረግ መተባበርና መሟገት እንደሚያስፈልግ የቤተክርስቲያን መሪው ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከቅጣትና ከበቀል ይልቅ በፈውስና በመረዳዳት ላይ የሚያተኩሩትን ዳግም የሚያድሱ የፍትህ ልማዶችን ለማስፋፋት ቤተክርስቲያን እና መንግስት በጋራ እንዲሰሩ አበረታተዋል።

ይህም አካሄድ ተጠቂውን፣ ወንጀለኛውን፣ የተጎዱትን እና ለአደጋ የተጋለጡትን በማገልገል አጠቃላይ የተሃድሶ እና የመልሶ ማቋቋም አቀራረብን ያመጣል ብለዋል።

ከፍርድ ቤት ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችን መከላከል
በሀገሪቱ የሞት ቅጣትን ለመሰረዝ የተካሄደው ወሳኝ እርምጃ የሰውን ልጅ ህይወት ቅድስና ለማስጠበቅ ትልቅ እርምጃ ነው በማለት የክርስትና እምነት መሰረታዊ መርሆ መሆኑን የገለጹት ጳጳሱ፥ ሆኖም ግን አሁንም ድረስ በዚምባብዌ ከፍርድ ቤት ውጭ የሚፈጸሙ ግድያዎች አሳሳቢ ናቸው ብለዋል።

የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ከህግ ማዕቀፎች ጋር በማጣመር፣ የቤተክርስቲያን እና የመንግስት ትብብር ማህበራዊ ኢፍትሃዊነትን መፍታት፣ ሰላምን ማስፈን እና ሰብአዊ መብቶችን የሚጠብቁ ፖሊሲዎችን ማጠናከር ይችላል ያሉት የዚምባብዌ ጳጳስ፥ “ይህ የህግ አስከባሪ ባለስልጣናትን በሰብአዊ መብቶች እና በህግ የበላይነት ላይ ማሰልጠን፣ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስን ማስተዋወቅ እና ከህግ አግባብ የግድያ ወንጀሎችን የሚዘግቡበት እና የሚመረመሩበትን ስልቶችን መዘርጋትን ሊያካትት ይችላል” በማለት ካብራሩ በኋላ፥ “ቤተክርስትያን የሞት ቅጣትን ትቃወማለች ምክንያቱም እስትንፋስን ወይም ህይወትን መልሶ የመውሰድ ስልጣን ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው” በማለት በአጽንኦት ገልጸዋል።

ከፍርድ ቤት ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችን የበለጠ ለመከላከል እና ይህንን ችግር ለመፍታት የትምህርት፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የሕክምና መርሃ ግብሮች መበረታታት እንዳለባቸው ሐሳብ ያቀረቡት ጳጳሱ፥ ይህ ትብብር የወንጀል መጠንን ለመቀነስ፣ ወንጀለኞችን ወደ ህጋዊ መንገድ መልሶ ለማቋቋም እና የሰውን ህይወት ዋጋ ለማስጠበቅ ይረዳል ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ሩዶልፍ ኒያንዶሮ በመጨረሻም የሞት ቅጣት መሰረዙ ሁሉም በጎ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ሊከበር የሚገባው እና ትልቅ ርህራሄ ያለው ማህበረሰብን የሚያጎለብት፣ በተሃድሶ ፍትህ እና በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ህይወት ዋጋ ላይ የሚደረገውን ውይይት የሚያበረታታ ነው በማለት አጠቃለዋል።
 

25 Feb 2025, 13:03