MAP

በሶሪያ ያሉ ክርስቲያኖች በገና ሰሞን የሚያሳይ ምስል በሶሪያ ያሉ ክርስቲያኖች በገና ሰሞን የሚያሳይ ምስል  (AFP or licensors)

በሶሪያ የሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ቁጥር እያነሰ መምጣት ትልቅ ጉዳት መሆኑ ተነገረ

የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት በሶሪያ ያለውን ሁኔታ በማንሳት፥ በተለይ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለው ነገር በጣም እንዳሳሰባቸው በመግለጽ የክርስቲያኑ ማህበረሰብ ከሀገሪቱ ‘መፈናቀል’ ለሶሪያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው እና ለዓለም መረጋጋት ‘አሳዛኝ ኪሳራ’ እና ትልቅ ጉዳት ነው በማለት አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የክርስቲያኑ ማህበረሰብ ከአከባቢው እየተሰደደ መምጣት ለሶሪያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሃገራት ብሎም ለዓለም መረጋጋት አሳዛኝ ኪሳራ እንደሆነ የገለጹት የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹእ አቡነ ማሪያኖ ክሮሺያታ ይሄንን ያሉት በሶሪያ ስላለው ሁኔታ በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።

የብጹእ አቡነ ክሮሺያታ መግለጫ የወጣው በሶሪያ የሆምስ ሃገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ዩሊያን ዣክ ሙራድ ለጻፉት ደብዳቤ ምላሽ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ብጹእ አቡነ ክሮሺያታ ከአስር ዓመታት በላይ ከቆየው ግጭት፣ ሁከት እና ስቃይ በኋላ፥ እንዲሁም አሁን ያለውን አለመረጋጋት በመገንዘብ በሶሪያ ውስጥ እየተካሄደ ላለው የሰብአዊ ቀውስ ጥልቅ ስጋት እንዳላቸው በማሳሰብ፥ አክለውም ሀገሪቱ በጀመረችው አዲስ ምዕራፍ ህዝቦቿ ተስፋ እንዳደረጉ ጠቁመው ይሄም ተስፋ ይሳካ ዘንድ ጸሎት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ለማሰብ የሚያዳግቱ መከራዎች

የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው የሶሪያ ህዝብ ሀይማኖት እና ጎሳ ሳይለይ “ለማሰብ የሚያዳግቱ መከራዎች” እንደገጠሟቸው በማስታወስ፥ መፈናቀልን፣ ድህነትን እና የመኖሪያ ቤቶቻቸው እና መተዳደሪያቸው ብሎም ማህበረሰባዊ ህይወታቸውም ጭምር እንደወደመ አንስተዋል። 

ብጹእ አቡነ ክሮሺያታ ከዚህም በተለየ ሁኔታ ለዘመናት የሃገሪቷ ታሪክ እና ባህል ዋነኛ አካል የሆኑትና በአሁኑ ወቅት በትውልድ አገራቸው ታሪካዊ ቀጣይነታቸውን ለማስጠበቅ እየታገሉ ያሉትን የሶሪያ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ችግር ትኩረት እንዲያገኝ ፍላጎቱ እንዳላቸው ከገለጹ በኋላ፥ አክለውም የአውሮፓ ህብረት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሶሪያ ክርስቲያን ማህበረሰቦችን ተጋላጭነት እንዲገነዘቡ አሳስበዋል።

መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማረጋገጥ
ከዚህም በተጨማሪ መግለጫው የሶሪያን ሕዝብ በተለይም ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን እና በቁጥር አናሳ የሆኑ ሃይማኖቶችን ጨምሮ ለችግር የተጋለጡትን የሶሪያን ሕዝብ ፍላጎት በሚያስቀድም መልኩ ጥበቃ፣ እንክብካቤ እና እድገት ለማረጋገጥ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወሰድ ጥሪ አቅርቧል።

ብጹእ አቡነ ክሮሺያታ አክለውም ይህ ኃላፊነት አፋጣኝ ሰብዓዊ ዕርዳታን ከማድረግ ባለፈ ለሰላም ግንባታ፣ ሃገሪቷን መልሶ ለመገንባት እና ለእርቅ የረጅም ጊዜ ስልቶችን ያካተተ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን እንደ ምግብ፣ መጠለያ፣ የጤና አጠባበቅ እንዲሁም የስነ ልቦና ፈውስ እና ትምህርትን ጨምሮ መሰረታዊ ፍላጎቶች ለሁሉም ሶሪያውያን መሟላታቸውን ለማረጋገጥ የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሀገራት ዘላቂ እና በቂ የገንዘብ ድጋፍ ለታመኑ አጋሮች እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

የአናሳ ማህበረሰቦችን መብቶች መጠበቅ
ጳጳሳቱም የግሉ ዘርፍ ተገቢውን ጥበቃና ዋስትና አግኝቶ በአገሪቱ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ማዕቀፍ እንዲፈጠር የጠየቁ ሲሆን፥ ብጹእ አቡነ ክሮሺያታ አክለውም የኮሚሽኑን አቋም ሲገልጹ፥ “በሶሪያ ህዝብ ደህንነት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ስለሚኖረው የአውሮፓ ህብረት በሶሪያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ቀስ በቀስ ለማቃለል የሚያደርገውን ውሳኔ በደስታ ይቀበላል” ብለዋል።

እንደ አውሮፓ ህብረት ጳጳሳት የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሀገራት በሶሪያ የሚገኙ አናሳ ማህበረሰቦችን መብት ለማስጠበቅ እንዲሰሩ የጠየቁት ጳጳሱ፥ “በህገ-መንግስታዊ ሂደቱ እና በመልሶ ግንባታው ውስጥ እንዲካተቱ እና እውቅና እንዲሰጣቸው ብሎም እንደ እኩል ዜጋ እንዲታዩ ያበረታታሉ” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሀገራቱ በሶሪያ የተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል ውይይትን፣ እርቅን እና ፈውስን የሚያበረታቱ ጅምሮችን እንዲደግፉ ጠይቋል።

የአውሮፓ ኅብረት ጳጳሳት “የቀድሞውን ሥርዓት ይደግፋሉ ተብለው በሚገመቱት ላይ የበቀል እርምጃ የመውሰድ አደጋ በሚፈጠርበት በዚህ ወቅት፣ ከበቀል መራቅና የሽግግር ሂደቱን ፍትሐዊና ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ተግባራዊ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስጠንቅቀዋል።

የቤተክርስቲያንን ድጋፍ ማረጋገጥ
ብጹእ አቡነ ክሮሺያታ ቤተክርስቲያኒቷ የሶሪያ ስደተኞችን እና ተፈናቃዮችን በተለይም ተሰደው የሚመጡትን ሰዎች መቀበል እና መደገፏን እንዲሁም በክብር እና በአግባቡ ማስተናገዷን ትቀጥላለች ብለዋል።

ብጹእነታቸው የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሀገራት ስደተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን በሰላም እና በፍቃደኝነት ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ለመፍጠር መስራት እንዳለባቸው በመግለጽ፥ “የአውሮፓ ህብረት ጳጳሳት እንደመሆናችን መጠን በሶሪያ ከሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በተለይም በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነት ከመሰከሩት የክርስቲያን ማህበረሰቦች ጋር አብረን እንቆማለን” ብለዋል።

መግለጫው በመጨረሻም ጳጳሳቱ ለሶሪያ ሰላም የፀሎት ጥሪ ማድረጋቸውን በመግለስ፥ ለወደፊት ሁሉም ሶርያውያን በነጻነት፣ በደህንነት እና በተስፋ የሚኖሩበት ሃገር እንድትሆን ‘ያለ እረፍት እንስራ’ በማለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፥ “የምህረት እናት የሆነችው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፥ የእግዚአብሔር የሰላም መሳሪያ እንድንሆን በተልእኮአችን ይምራን” በማለት በጸሎት አጠናቀዋል።
 

21 Feb 2025, 13:55