ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ የሰው ሰራሽ አብርኾት 'በሰው ቁጥጥር ሥር መሆኑን አረጋግጡ' ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የውሳኔ ሰጭዎች የሰው ልጅ የ AI (የሰው ሰራሽ አብርኾት) የውሳኔ አሰጣጥ አቅሞችን በቂ ቁጥጥር እንዲያደርጉ እና AI በሰዎች ግንኙነት፣ መረጃ እና ትምህርት ላይ ያለውን ተፅእኖ በጊዜ ሂደት እንዲመረምሩ ጠይቀዋል።
ቅዱስ አባታችን ይህን ያሉት ከየካቲት 03-04/2017 ዓ.ም በፓሪስ በተካሄደው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የድርጊት ጉባኤ ላይ ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በላኩት መልእክት ነው። በመልእክቱ ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "ምስጋና የሚገባው ተነሳሽነት" ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፣ እናም ተጨባጭ ውጤቶችን ለማምጣት በሚያስችል ነጸብራቅ ውስጥ በተቻለ መጠን እጅግ በጣም ብዙ ተዋናዮችን እና ባለሙያዎችን ለማካተት ያደረጉት ጥረት የምያስመሰግን ነው ብለዋል።
ለመሣሪያው ማለትም ለሰው ሰራሽ አብርኾት ቴክኖሎጂ ያላቸውን አድናቆትና መልካም ለማድረግ ያለውን አቅም በመግለጽ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ AI ትክክለኛ የሰው ቁጥጥር ከሌለው፣ “በሰው ልጅ ክብር ላይ ስጋት በመፍጠር እጅግ ‘አስፈሪ’ ጎኑን ሊያሳይ ይችላል” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው በመልእክታቸው ገልጸዋል።
“ስለዚህ የሰው ልጅን ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አብርኾት) ለመከላከል ያለመ የፖለቲካ ሂደት በድፍረት እና በቁርጠኝነት ለመጀመር እየተካሄደ ያለውን ጥረት አመሰግናለሁ፣ እናም የዓለም አተያያችንን በቁጥር ሊገለጽ በሚችል እና አስቀድሞ በተወሰነ ምድቦች ውስጥ በተካተቱ እውነታዎች ላይ ሊገድብ ይችላል” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ።
አልጎሪዝም እና ልብ
ቅዱስ አባታችን ባስተላለፉት መልእክት፣ ጉባኤው በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አብርኾት) ላይ የሕዝብ ጥቅም መድረክ ለመፍጠር እንደሚሠራ፣ “ማንኛውም ሕዝብ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውስጥ ለልማቱና ድህነትን ለመታገል የሚረዳ መሣሪያ እንዲያገኝ፣ የአካባቢ ባሕልና ቋንቋዎች ጥበቃ እንዲደረግለትም እንደሚሠራ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ መንገድ ብቻ፣ በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሕዝብ ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አስተዋፅዖ ማድረግ የሚችለው “የሰው ልጅ ቤተሰባችን መለያ የሆነውን እውነተኛ ልዩነትና ብልጽግናን ያንጸባርቃል” ብሏል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቅርቡ በአልጎሪዝም አሠራር እና በ "ልብ" ኃይል መካከል ያለውን ልዩነት አስታውሰዋል።
"አልጎሪዝም ለማታለል እና ለማሳሳት ጥቅም ላይ ሊውል ቢችልም፣ እንደ ጥልቅ እና ትክክለኛ ስሜታችን መቀመጫ የተረዳው ልብ በጭራሽ ሊያታልል አይችልም" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
ኃይል ለሰው ልጅ ለበጎ ተግባር ሊውል ይገባል
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተመለከቱት ከሆነ፣ “የጋራ ቤታችን የሆነውን የምድርን ሥነ-ምህዳራዊ ዘላቂነት የሚያበረታቱ አዳዲስ እና ፈጠራዊ መፍትሄዎችን ለማግኘት በሚተባበሩ ሳይንቲስቶች እና ባለሙያዎች እጅ ውስጥ ኃይለኛ መሣሪያ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል ፣ “ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረተ ልማቶች አሠራር ጋር የተያያዘውን ከፍተኛ የኃይል ፍጆታን ችላ ማለት አይቻልም" ያሉ ሲሆን በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቁጥጥር “ድሆችን፣ አቅመ ደካሞችን እና ሌሎች በአለም አቀፍ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ብዙ ጊዜ የማይሰሙትን ጨምሮ” በሚደረጉ ክርክሮች ላይ የባለድርሻ አካላት ድምጽ ግምት ውስጥ እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የእኛ የመጨረሻ ፈተና ሁሌም የሰው ልጅ ሆኖ ይቀራል። ይህን መቼም እንዳንረሳው!” በማለት አጽንኦት ሰጥተወ በመልእክታቸው ከገለጹ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠቃለዋል።