MAP

ክቡር አባ መርሃክርስቶስ (ጎበዝአየሁ) ጌታቸው ይልማ  ክቡር አባ መርሃክርስቶስ (ጎበዝአየሁ) ጌታቸው ይልማ  

የክቡር አባ መርሃክርስቶስ (ጎበዝአየሁ) ይልማ (ዶ/ር) ሢመተ ጵጵስና በሃዋሳ ሃገረስብከት ኪዳነምህረት ካቴድራል ተካሄደ

የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ክቡር አባ መርሃክርስቶስ (ጎበዝአየሁ) ጌታቸው ይልማ በሃዋሳ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሃገረስብከት ውስጥ በሚገኘው ኪዳነምህረት ካቴድራል በብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን በተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ ሢመተ ጵጵስናቸው ተፈፅሟል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ክቡር አባ ጎበዝአየው ጌታቸው ይልማን የሐዋሳ አገረ ስብከት ጳጳስ አድርገው ህዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን፥ የሐዋሳ አገረ ስብከት ላለፉት 4 ዓመታት ያህል ያለ ጳጳስ በኢትዮጵያ የኮንቦኒ ማሕበር አባላት ካህናት ድጋፍ ሲተዳደር የነበረ አገረ ስብከት እንደሆነም ይታወቃል።

የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. የሐዋሳ ሀገረ ስበከት ለእጩ ጳጳስ አባ ጎበዝአየሁ ጌታቸው ደማቅ አቀባበል ያደረገ ሲሆን፥ በዚህ ሥነ ስርዓት ላይ ብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ በርካታ መዘምራን እና ምዕመናን፣ የተለያዩ ቤተ ዕምነት ተወካዮች፣ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ እና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የተሰባሰቡ እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል። መርሃግብሩ ጥቁር ውሃ ከሚገኘው የቅዱስ ዮሀንስ 23ኛ የህንጸት ማዕከል በመዘምራን፣ በምዕመናን እና በማርሽ ባንድ በመታጀብ ወደ ሐዋሳ ኪዳነምህረት ካቶሊክ ካቴድራል በማቅናት የጸሎት መርሃግብር በማድረግ ተካሂዷል።

በዋዜማው መርሃግብር ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ የደስታ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ቤተክርቲያናችን በተለይም በሐዋሳ የሚገኙ ካቶሊካውያን ላለፉት አራት ዓመታት በጸሎት ሲጠብቁ የነበረውን የሰበካውን እረኛ ጳጳስ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ክቡር አባ ዮሀንስ በነዚህ አራት ዓመታት ሰበካውን በሐዋርያዊ አስተዳደርነት ሲመሩ መቆየታቸው የተገለጸ ሲሆን ላበረከቱትም የላቀ አስተዋጽዖ የሀገረስብከቱ የልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አባ ጸጋዬ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ክቡር አባ ጎበዝአየው ጌታቸው ይልማ በኦሮሚያ ክልል ዶዶላ (ባሌ ዞን) በተባለ ቦታ እ.አ.አ ታኅሣሥ 4 ቀን 1978 ዓ.ም. የተወለዱ ሲሆን፥ በጅማ የግብርና ዩኒቨርሲቲ የግብርና ትምህርታቸውን ተከታትለው በማጠናቀቅ፣ በመቀጠልም በአዲስ አበባ ከሚገኘው ካፑቺን ፍራንችስካዊያን የነገረ መለኮት ኢንስቲትዩት የፍልስፍና እና ነገረ-መለኮት ትምህርት ተምረው አጠናቀዋል። ከዚህም ባሻገር ከሮማ ጳጳሳዊ ኡርባኒያና ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና ዲፕሎማ እና በነገረ መለኮት ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ዕጩ ጳጳስ ክቡር አባ ጎበዝአየው ጌታቸው ጥር 16 ቀን 1997 ዓ.ም ማዕረገ ክህነት የተቀበሉ ሲሆን፥ በአገልግሎት ዘመናቸው በተለያዩ ቦታዎች አገልግለዋል። ከእነዚህም መካከል በርካታ የኃላፊነት ቦታዎችን በመያዝ ተጨማሪ ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ ተግባራትን አከናውነዋል። ከ 1996 – 1997 ዓ.ም. የመቂ ሃገረ ስብከት (ቫካሪየት) ጸኃፊ እና የወጣቶች አስተባባሪ ምክትል ዋና ጸሐፊ፣ እንዲሁም ከ 1998 – 2001 ዓ.ም. ድረስ የመቂ ካቶሊክ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል።

ክቡር አባ ጎበዝአየሁ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በመቀጠል ከ 2001 – 2007 ዓ.ም. ድረስ ደብሊን ከሚገኘው የኪሜጅ ልማት ጥናት ማዕከል በልማት ጥናት የማስትሬት ድግሪ እንዲሁም ከሜይኖዝ ቅዱስ ፓትሪክ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ በሥነ መለኮት እና በካቶሊክ ማህበራዊ አስተምህሮ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። አባ ጎበዝአየሁ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የመቂ አገረ ስብከት ጳጳስ ጸኃፊ እና በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚተዳደረው ካሪታስ (የመቂ ካቶሊካዊ ጽሕፈት ቤት) ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል።

ባለፉት ወራት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አዲስ ከተሾሙት ዕጩ ጳጳሳት መካከል የሙስሊም ማህበረሰብ በሚበዛበት ክልል ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት ክቡር አባ ጎበዝአየሁ ጌታቸው ቤተክርስቲያኒቷ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት እና የክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ተነሳሽነቶችን ለማሳደግ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በክቡር አባ ጎበዝአየሁ (መርሃክርስቶስ) ጌታቸው ይልማ የጵጵስና መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት፣ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ ከተለያዩ ሀገራት የተወከሉ የማህበራት ልዑካን አለቆች፣ የሌሎች ሀይማኖት ተወካዮች፣ የመንግስት ተወካዮች፣ በርካታ ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ምዕመናን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
 

10 Feb 2025, 13:41