MAP

መንፈሳዊ ነጋዲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቤቴልሄምን ሲጎበኙ  መንፈሳዊ ነጋዲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቤቴልሄምን ሲጎበኙ   (ANSA)

የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ከምስራቃውያን አቢያተ ክርስቲያናት የወጡ ዜናዎች

በዚህ ሳምንት ከምስራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት የወጡ ዜናዎች እንደሚያመላክቱት አዲስ የአሦር ካቴድራል በለንደን መከፈቱን፣ አርመኖች የቅዱስ ሳርጊስን በዓል ማክበራቸውን እና በቤተልሔም የቅርስ ኮንፈረንስ መካሄዱን ጠቁመዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከ170 ለሚበልጡ ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ በምሥራቅ አውሮፓ እና በህንድ ከሚገኙ 23 አገሮች የተውጣጡ ምስራቃውያን ክርስቲያኖችን ሲረዳ ከቆየው ‘ሎውቭር ዲ ኦሪየንት’ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ዘገባ በዚህ ሳምንት በምስራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የተካሄዱ ዜናዎችን ይፋ አድርጓል።

በለንደን የሚገኘው የአሦር ቅድስት ማርያም ካቴድራል ምረቃ
እሑድ የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የምስራቅ አሦር ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ይሆኑት ብፁዕ አቡነ ማር አዋ ሣልሳዊ እና ብጹእ አቡነ ማር አውራሃም ዮካኒስ በጋራ በመሆን በለንደን የሚገኘውን አዲሱን የቅድስት ማርያም ካቴድራል መርቀዋል። በእንግሊዝ፣ በፈረንሣይ፣ በቤልጂየም፣ በኦስትሪያ፣ በኔዘርላንድስ እና በግሪክ የሚገኙ ደብሮችን የሚያጠቃልለው ይህ ካቴድራል በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ሀገረ ስብከት መቀመጫ ሆኖ እንደሚያገለግል የተገለጸ ሲሆን፥ በቀድሞ ጊዜ የቅዱስ ያዕቆብ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን የነበረው ሕንፃው በ 2010 ዓ.ም. በደረሰበት መዋቅራዊ እክል ምክንያት ተዘግቶ እንደነበር ይታወሳል። በአካባቢው በሚገኙ የአሦር ማህበረሰብ እና ዲያስፖራዎች በተደረገው ድጋፍ ህንፃው ተገዝቶ እድሳት ከተደረገለት በኋላ አሁን ላለበት ደረጃ መድረሱ የተነገረ ሲሆን፥ በዩናይትድ ኪንግደም ያለው የአሦር ማህበረሰብ ወደ 7,000 ያህል እንደሚገመትም ተገልጿል።

የቅዱስ ሳርጊስ በዓል በአርሜኒያ
ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. የአርመናዊያን ሐዋርያዊ ሃገረ ስብከቶች እና ካቶሊካዊያን ምዕመናን የቅዱስ ሳርጊስን በዓል አክብረው የዋሉ ሲሆን፥ የአርሜኒያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ካቶሊካዊያን አርመኖች ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ፓትሪያርክ ካሬኪን ሁለተኛ ይህ ክብረ በዓል የወጣቶች የበረከት ቀን ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል።

በዚህ ክብረ በዓል ላይ በመላ አርመኒያ የሚገኙ ከተለያዩ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ ወጣቶች በዋናው የኤቸ-ሚያዚን ካቴድራል ተገኝተው እንዳከበሩ ተገልጿል።

የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕት እና የቀድሞ የባይዛንታይን ጄኔራል ቅዱስ ሳርጊስ የወጣትነት ጠባቂ ተብሎ የሚከበር ሲሆን፥ በባህሉ መሠረት ወጣቶች የወደፊት የትዳር አጋሮቻቸውን ለማግኘት ለሰማእቱ ጸሎት የሚያደርጉበት እና ሕልማቸው የወደፊት ፍቅራቸውን እንደሚገልጥ ተስፋ በማድረግ ከመተኛታቸው በፊት አግሃ-ብሊት በመባል የሚታወቁትን ጨዋማ ብስኩቶች የሚመገቡበት ቀን እንደሆነም ተገልጿል።

የቅድስት ሀገር ቅርሶችን አስመልክቶ የተካሄደ ጉባኤ
የካቲት 7 እና 8 በአል-ሊቃ የሃይማኖት፣ የቅርስ እና የባህል ጥናት ማእከል አዘጋጅነት ለሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች 30ኛው የአረብ ቅርስ ጉባኤ በቤተልሔም ተካሂዷል። የዘንድሮው ጉባኤ መሪ ቃል “ፍትህ የሰላም መንገድ ነው” የሚል ሲሆን፥ በዝግጅቱም ላይ ካህናት፣ ምሁራን እና ተመራማሪዎች መገኘታቸው ተነግሯል።

በጉባኤው ላይ የተካሄዱት ውይይቶቹም በመካሄድ ላይ ያሉት ጦርነቶች በሚያደርሱት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተፅእኖ ላይ ያተኮሩ ሲሆን፥ በየቀኑ ከቱሪዝም ገቢ ይገኝ የነበረው 2.5 ሚሊዮን ዶላር በጦርነቱ ምክንያት እንደቀረ እና በቤተልሔም የሥራ አጥ ቁጥሩ በ36 በመቶ መጨመሩ የተገለጸ ሲሆን፥ በክርስቲያን ተቋማት ላይ ያለው የገንዘብ ጫና እና የብዙ ፍልስጤማውያን ስደት ቁልፍ የክርክር ርዕሰ ጉዳዮችም እንደነበሩ ተመላክቷል።
 

24 Feb 2025, 14:17