MAP

ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም.  የጀርመን የክርስቲያን ዲሞክራሳዊ ህብረት ፓርቲ ጉባኤውን በሚያካሂድበት ወቅት በተዘጋጀው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሰዎች የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. የጀርመን የክርስቲያን ዲሞክራሳዊ ህብረት ፓርቲ ጉባኤውን በሚያካሂድበት ወቅት በተዘጋጀው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሰዎች የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው   (AFP or licensors)

የጀርመን ሚስዮናውያን ለስደተኞች እና ለአየር ንብረት እርምጃ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቀረቡ

የጀርመን ፓርላማ ምርጫ እየተቃረበ በመጣበት በአሁኑ ወቅት በሃገሪቷ ውስጥ የሚገኙ ሚስዮናውያን ‘ቡንደስታግ’ ተብሎ የሚጠራው የፓርላማ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት እጩዎች የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የስደትን ዋና ዋና መንስኤዎች ለመዋጋት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጀርመን መጪው የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ወሳኝ የሆነ የፌደራል ምርጫ ለማድረግ እየተዘጋጀች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የጀርመን ሚስዮናውያን በቋሚነት በሰብአዊ መብቶች ላይ የተመሰረቱ እና የህዝቡን መሰረታዊ የረዥም ጊዜ ጥቅም የሚያስከብር የስደት እና የልማት ፖሊሲዎች እንዲያወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ስደተኞች መንስኤዎቹን እንዲዋጉ ካልተፈለገ
የሚስዮናውያን ማህበር ጉባኤ (KMO) ለዋና ዋና እጩዎች በላከው ግልጽ ደብዳቤ ላይ ፖለቲከኞች ችግር ላይ ያተኮረ ሳይሆን ሰዎችን ያማከለ የስደተኞችን ራዕይ መደገፍ አለባቸው ብሏል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት በሆኑት ኡርሱላ ሹልተን እንዲሁም የቦርድ አባላት በሆኑት የሳሌዥያን ካህን አባ ራይንሃርድ ጌሲንግ እና እህት ቦስኮ ቢርጊት ባየር በተፈረመበት ደብዳቤ “ስደተኞችን ካልፈለጋችሁ መንስኤዎቹን ለመከላከል የበለጠ ጥረት ማድረግ አለባችሁ” በማለት አሳስቧል።

በጀርመን የምርጫ ዘመቻ ማዕከል የሚነሱ የስደት ጉዳዮች
መጀመሪያ ላይ መስከረም 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ታቅዶ የነበረው በጀርመን የሚካሄደው የፌደራል ምርጫ በቅርብ ጊዜ በሶሻል ዴሞክራት ኦላፍ ሾልስ የሚመራው የመንገድ መብራት አስተዳደር ጥምረት በመፍረሱ ምክንያት ምርጫው ቀረብ ብሎ እንዲደረግ ተወስኗል።

እንደሌሎች አውሮፓውያን እና ሌሎች አከባቢዎች ሁሉ የስደት ህግ በጀርመን ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሲሆን፥ በዚህ ምርጫ ዋነኛው ተፎካካሪ የሆነው ‘ኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመኒ’ (AFG) የተባለው የቀኝ ዘመም ፓርቲ ስደተኞችን በብዛት ለማባረር ቃል በመግባት የምርጫ ቅስቀሳውን እያደረገ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በስደት ዙሪያ ያለው ስጋት ጨምሯል
በቅርቡ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰቱት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ያካተተው አደገኛ እና ሞትን ያስከተሉ ጥቃቶች በስደት ዙሪያ ያለውን ፍራቻ በማባባስ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥብቅ የስደት ፖሊሲዎችን እንዲያወጡ መነሻ እንደሆናቸው ብሎም የኤ. ኤፍ. ዲ. ፓርቲ ደጋፊዎችን እንዳበዛ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም በላይ በአሁኑ ጊዜ ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ (CDU/CSU) ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ተነግሯል።

የክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ ከፍተኛ እጩ የሆኑት ቻንስለር ፍሬድሪች ሜርዝ ባልተጠበቀ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት ከኤ.ኤፍ.ዲ. ፓርቲ ጋር በመተባበር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ እንደ ሰብዓዊ ጥሰት የሚቆጠረውን የፀረ-ኢሚግሬሽን ውሳኔን ለማፅደቅ በመሞከራቸው በመላው ጀርመን ሰፊ ተቃውሞ አስነስቷል።
ከዚህም ባለፈ ይህን እርምጃ የጀርመን የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ እና የሉተራን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ከአይሁድ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን በጋራ ተቃውመውታል።

የሚሲዮናዊያን ማህበራት ጉባኤ ‘ወደ አውሮፓ የሚመጡት ስደተኞች ጥቂት ናቸው’ ማለቱ
የጀርመን ሚስዮናውያን ማህበራት ጉባኤ በፃፉት ደብዳቤ ላይ ስደትን እንደ ብሔራዊ ደህንነት ስጋት ተደርጎ በሚነገረው ትርክት ላይ ያላቸውን ጥልቅ ስጋት በመግለጽ፥ ከደቡብ የዓለም ክፍል በተለያየ ምክንያት ቤታቸውን ለቀው ወደ አውሮፓ ለመሰደድ የሚገደዱት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ለእጩዎች በማሳሰብ፣ “አብዛኞቹ ከአውሮፓ መንግሥታት ይልቅ ከፍተኛ የሆነ የስደት ጫናን ወደሚያስተናግዱ ጎረቤት አገሮች ይሸሻሉ” በማለትም ገልጿል።

የፓርላማ ምርጫው በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት ስለ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የተሳሳተ መረጃ በጀርመን ማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እየተሰራጨ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ።

ስደተኞችን ለመቀነስ አስቸኳይ የሆነ የአየር ንብረት እርምጃ ያስፈልጋል
ደብዳቤው ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው እነዚህ ስደተኞች የአየር ንብረት ለውጥ ውጤት ሰለባዎች መሆናቸውን በመግለጽ “እኛ በሰሜናዊ የዓለም ክፍል የምንገኝ በሙሉ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂዎች ነን” በማለትም አስታውሷል።

በመሆኑም የጀርመን ሚስዮናውያን ማህበራት ጉባኤ እጩዎቹ ጀርመን ድሀ ሀገራትን የመደገፍ ያላትን ታሪካዊ ሃላፊነት በይፋ እንዲገነዘቡ እና መሰረታዊ መብቶቻቸው የሚጣሱ ሰዎችን እንዲደግፉ ካሳሰቡ በኋላ፥ “እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በሚሊዮኖች እና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሕልውና ሁኔታ አደጋ ላይ እየጣልን ነው የሚለውን ሳይንሳዊ መሰረት ያለው እውነት ተቀብላችው የአገራችንን ህዝብ ለመታደግ ድፍረት ሊኖራችሁ ይገባል፥ ይህ ካልሆነ ግን የራሳችን ብልጽግናም አደጋ ላይ ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።

ሃይማኖታዊ ማህበራቱ በበኩላቸው ‘በአገራችን እና በደቡቡ የዓለም ክፍል በሚገኙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለማገልገል በሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን የማህበራዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥ” ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የሚስዮናውያን ማህበር ጉባኤ በጀርመን የሃይማኖታዊ የበላይ ተቆጣጣሪዎች ጉባኤ (DOK) ውስጥ በዓለም ዙሪያ የሚሰሩ 92 ሃይማኖታዊ ማህበራትን በአንድ ላይ ያሰባሰበ ተቋም ሲሆን፥ እነዚህ ማህበራት የአየር ንብረት ለውጥ በሚያገለግሉበት የደቡቡ የዓለም ክፍል ውስጥ በሚገኙ ህዝቦች ላይ እያሳደረ የሚገኘውን ከባድ ተጽዕኖንም እንደሚረዱ ተገልጿል።
 

06 Feb 2025, 13:40