MAP

የባሪያ ነጋዴዎች ባሪያዎችን ያጓጉዙበት ወደ ነበረው የጋምቢያ ሰሜናዊ ዳርቻ ወደሆነችው ጁፈሬህ ከተማ፣ አልብሬዳ መንደር የሚገኘው የጸረ-ባርነት ሀውልት   የባሪያ ነጋዴዎች ባሪያዎችን ያጓጉዙበት ወደ ነበረው የጋምቢያ ሰሜናዊ ዳርቻ ወደሆነችው ጁፈሬህ ከተማ፣ አልብሬዳ መንደር የሚገኘው የጸረ-ባርነት ሀውልት  

የእምነት ማህበረሰቦች ለአፍሪካ ፍትህ እየተሟገቱ እንደሆነ ተነገረ

የአፍሪካ ሀገራት እና አፍሪካዊ ተወላጆች የዘር መድልዎ፣ ኢኮኖሚያዊ መገለል እና የእኩልነት መጓደል እየደረሰባቸው ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ በርካታ የእምነት ማህበረሰቦች ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ በትምህርት እና በህግ ማሻሻያ በኩል ፍትህ እንዲሰፍን ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በአፍሪካ አህጉር እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ የሚገኙት እና በከፍተኛ ሁኔታ ስር እየሰደደ የመጣውን የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ፣ ባርነት፣ ቅኝ ግዛት እና ኢ-ፍትሃዊ የእኩልነት ችግር ለመፍታት ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ የሀይማኖት እና የስነ-ምግባር መሪዎች በኢትዮጵያ በመሰባሰብ፣ በአህጉሪቱ በተከሰቱት ኢፍትሃዊ ድርጊቶች ምክንያት ለሚደርሰው ጉዳት ፈውስ እና ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ በመምከር ላይ ይገኛሉ።

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚየም (SECAM) በሰጠው መግለጫ የካቲት 27 እና 28 ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው አውደ ጥናት “በእምነት ማህበረሰቦች እና በሕዝብ መካከል ስላለው ፍትህ” ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ አውደ ጥናቱ “ለዚህ ዓላማ የተሠማሩ የእምነት እና የሥነ ምግባር ድርጅቶች ጥምረት ለመመስረት እና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር የፖሊሲ ምክሮችን እና የተግባር ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ያለመ ነው ተብሏል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ፖሊሲ አውጭዎች የተሳተፉ ሲሆን፥ ጉባኤውን ያዘጋጁት የአፍሪካ እና የማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚየም፣ በአፍሪካ ኅብረት የካቶሊክ ካህናት ማህበር፣ የሰማያዊ ባህል፣ የዓለም ሰላም እና የብርሃን ተሃድሶ ተቋም፣ የፓን አፍሪካ የሥነ ምግባር ጉባኤ እና የሃይማኖት ተቋማት የሰላም እና ልማት ማኅበር፣ የተባበሩት የሃይማኖት ተቋማት ንቅናቄ እና ሌሎች ቁልፍ አጋሮች ከዜጎችና ዳያስፖራ ኅብረት ዳይሬክቶሬት ኮሚሽነር ጋር በመተባበር እንደሆነ ተገልጿል።

ለፍትህ የተደረገ ጥሪ

አፍሪካ መጪው ዘመኗ በፍትሃዊነት፣ በእኩልነት እና በብልጽግና የተሞላ መሆኑን ለማረጋገጥ እምነት ላይ የተመሰረቱ እና ሥነ ምግባር ያላቸው ማህበረሰቦች ተጨባጭ ተግባር እና ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት በጋራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ያሳወቁ ሲሆን፥ “ለዘመናት አፍሪካውያን እና የአፍሪካ ተወላጆች ታሪካዊው ኢፍትሃዊነት ማለትም ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ማጣት፣ ማህበራዊ መገለል እና የስነ-ልቦና ጉዳትን የሚያስከትለውን የኢ ፍትሃዊነት መዘዞችን ተቋቁመው ኖረዋል” በማለት ገልጸዋል።

“የባርነት፣ የቅኝ ግዛት፣ የአፓርታይድ እና የዘር ማጥፋት ትሩፋቶች ዛሬም ማህበረሰቦቻችን ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ቀጥለዋል” በማለት የገለጸው የሴካም መግለጫ፥ ይህንን በመገንዘብ የአፍሪካ ኅብረት እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ፖሊሲዎች፣ ቅስቀሳዎችን እና ዓለም አቀፍ ተሳትፎን በማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብሏል።

የአፍሪካ እና የማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ኃላፊዎች እንዳስታወሱት ጋና ከዚህ ቀደም በ 2011 ዓ.ም. “የመመለሻ ዓመት” በሚል መሪ ቃል ባካሄደችው ዘመቻ በኩል ለዚህ ዓላማ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳበረከተች ጠቁመዋል።

አውደ ጥናቱ “ፍትሕን ለማስፈን በእምነት ላይ የተመሰረቱ እና በሥነ ምግባር የታነጹ ድርጅቶችን ድምፅ በማጉላት እንዲህ ያለውን ጥረት ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ጭምር ተብራርቷል።

በኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በሚገኘው ኩሪፍቱ ሪዞርት የአፍሪካ መንደር እና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የተካሄደው አውደ ጥናት የአፍሪካ ህብረት በአውሮፓዊያኑ 2025 “ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ለአፍሪካ ተወላጆች በጥገናዊ ፍትህ በኩል” በሚል መሪ ሃሳብ ጋር እንደሚጣጣም የተነገረ ሲሆን፥ የአውደ ጥናቱ አዘጋጆች ከአፍሪካ ህብረት እና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በእምነት ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች ለአፍሪካውያን እና አፍሪካውያን ተወላጆች ፍትህ እና ካሳ የለውጥ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
 

28 Feb 2025, 13:28