MAP

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባንዲራዎች በቡካቩ ኤም 23 ምስራቃዊ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ ሲውለበለቡ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባንዲራዎች በቡካቩ ኤም 23 ምስራቃዊ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ ሲውለበለቡ   (AFP or licensors)

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጳጳሳት ግጭትን እና ቋንቋን መሰረት ያደረገ መድልዎን አወገዙ

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብጹአን ጳጳሳት በቋንቋ ላይ የተመሰረተ አድሎአዊ ድርጊትን፣ በተለይም በኮንጎ ስዋሂሊ ተናጋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን መድሎ በማውገዝ፥ በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክልሎች እየተካሄደ ያለው ግጭት መከፋፈልን እያመጣ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ የኤም 23 አማፂ ቡድን በማዕድን የበለፀገውን ምስራቃዊ የኮንጎ ግዛቶች ፈጣን በሆነ ግስጋሴ መቆጣጠሩን ተከትሎ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው ውጥረት ወደ ላቀ ደረጃ እየደረሰ እንደሚገኝ ተነግሯል።

ግጭቱ እየተስፋፋና ፍርሃቱ ህብረተሰቡን እያስጨነቀ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት በቋንቋ ልዩነት ላይ የተመሰረተ አድሎአዊ እና መከፋፈል እንዳይስፋፋ አስጠንቅቀዋል።

የኮንጎ ብሔራዊ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት ብሔራዊ አንድነት ወሳኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ቋንቋን መሰረት ያደረገ አድልዎ ወደ ጥልቅ ማኅበራዊ ስብራት እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቀዋል።

“በአገራችን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል የሚኖሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በተለይም በሰሜን እና በደቡብ ኪቩ አውራጃዎች ውስጥ ጦርነቱ በአስከፊ ሁኔታ እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በቋንቋ አገላለጽ ላይ የተመሰረተ ጥቃት እያገረሸ መጥቷል” በማለት የኮንጎ ብጹአን ጳጳሳት የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የቤተክርስቲያን መሪዎቹ በመግለጫቸው አንዳንድ ኮንጎያውያን ከብዙ የአካባቢ ዘዬዎች ጋር በጥምረት የሚነገር እና ከአገሪቱ አራት ብሔራዊ ቋንቋዎች አንዱ የሆነውን የስዋሂሊ ቋንቋ የሚናገሩ ዜጎቻቸውን በማጥላላት ላይ መሆናቸውን በምሬት በመግለጽ፥ እየተደረገ ያለውን ድርጊት “የስዋሂሊ ተናጋሪዎችን ማደን ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

የሃይማኖት መድረኮችን አላግባብ መጠቀም
እንደ ብጹአን ጳጳሳቱ ገለጻ አንዳንድ “ፓስተሮች” በቤተ ክርስቲያን መድረኮችና ሌሎች ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች ላይ መለያየትን በማስፋፋት ማኅበራዊ አንድነትን በማፍረስ እንዲሁም አንድነትን፣ ሰላምንና አብሮ መኖርን የሚያጎለብቱ መሠረታዊ የእምነት መርሆችን እየከዱ ነው በማለት ገልጸዋል።

የኮንጎ ብሔራዊ የብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት እንደገለጹት አንዳንድ ‘ፓስተሮች’ በቤተ ክርስቲያኖቻቸው መድረክ እና በሌሎች የስብከት ቦታዎች ላይ በሌሎች የኮንጐላውያን ወንዶችና ሴቶች ላይ በትውልድ፣ በቋንቋ ወይም በሥርዓተ ባሕሪያቸው ምክንያት አድልዎን፣ ጥላቻን እና ጥቃትን የሚቀሰቅሱ ንግግሮችን ሲጠቀሙ ማየታቸው የበለጠ እንዳሳዘናቸው እና እንዳስቆጣቸው ጭምር ገልጸዋል።

ወደ ማህበራዊ አንድነታችን እንመለስ
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለበርካታ አስርት ዓመታት ብጥብጥ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና የጎሳ ግጭቶች በተደጋጋሚ ቢያጋጥሟትም፥ ብጹአን ጳጳሳቱ ቀደም ሲል የኮንጎ ዜጎች ከተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች መሪዎችን በመምረጥ አንድነታቸውን ያሳዩበትን ሁኔታ መቀበል እና በዚሁ ሁኔታ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ጳጳሳቱ የማዕከላዊ ኮንጎ ግዛት ተወላጅ የሆኑ የጎማ ገዢ እና ብሔራዊ ምክትል በመሆን በጋራ የተመረጠበትን ጊዜ በመጥቀስ፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ለሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንትነት ከምዕራብ እና ከምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል የተወከሉ እጩ ተወዳዳሪዎች ከሁለቱም ወገኖች መመረጣቸውን አስታውሰው፥ “ዛሬ በሚያሳዝን ሁኔታ እኛን ሊያሳስበን የማይገባ የነበረ እና ወደ ኋላ የሚጎትት ነገር እያጋጠመን ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ብስለት እና አብሮነት
ብጹአን ጳጳሳቱ ሁሉም ዜጋ የአስተሳሰብ ብስለት ሊኖረው እና መተሳሰብ እንደሚገባው ያሳሰቡ ሲሆን፥ በአገር ፍቅር ሽፋን መድሎን ማስፋፋት የሀገር አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥል እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት የሚጎዳ መሆኑን በማስጠንቀቅ፥ በጦርነት እና በጸጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች አጋርነት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

መግለጫው የአገር ፍቅር መገለጫ እና ለሀገሪቷ የሰላም ጎዳና እንደሆነ በማስመሰል መለያየትን እንዲሁም የስዋሂሊ ተናጋሪዎችን፣ የምስራቅ ተወላጆችን ወይም የውጭ አገር ዜጎችን የሚጎዳ ነገር በሚሰብኩ ሰዎች ህዝቡ እንዳይሳሳት በማሳሰብ፥ በጦርነት እና በሰላም እጦት ተገደው መሬታቸውንና ቤታቸውን ለቀው ለተሰደዱ ወንድሞች እና እህቶች ህዝቡ ርህራሄ እና አጋርነት እንዲያሳይ ብሎም እንደ ቤተሰቦቻቸው አድርገው በአስተማማኝ ቦታ እንዲያስተናግዷቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ በመጨረሻም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና ለሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ማህበራዊ ትስስር እና መልካም ኑሮ እንዲኖር መንግስት ሙሉ ሀላፊነቱን እንዲወስድ በመጠየቅ አጠቃለዋል።
 

27 Feb 2025, 13:04