MAP

የቅዱስ ቁርባን ስግደት፥ ሮም በሚገኘው ጀሜሊ ሆስፒታል የቅዱስ ቁርባን ስግደት፥ ሮም በሚገኘው ጀሜሊ ሆስፒታል  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጀሜሊ ሆስፒታል የዕለታዊ ስግደት እና የቅዳሴ ሥነ ስርዓት እየተደረገ ይገኛል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ህክምናቸውን እየተከታተሉበት ባለው ሮም በሚገኘው ጀሜሊ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እና ታማሚዎች በየቀኑ የአንድ ሰዓት የቅዱስ ቁርባን ስግደት እና መስዋዕተ ቅዳሴ በማቅረብ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ያላቸውን አጋርነት እየገለጹ ይገኛሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ባልዳሳሬ ሬይና የጣሊያን ብጹአን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ ሁሉም ሰው እንዲጸልይላቸው ያበረታቱ ሲሆን፥ “የጋራ ጸሎት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በመገንዘብ፣ በየቁምስናው የሚገኙ ሁሉም ምዕመናን እና ሃይማኖታዊ ማህበረሰቦች ለብጹእ አባታችን ጤንነት በጥሞና የተሞላ የአንድ ሰዓት ስግደት እና ጸሎት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህንን የጋራ ጸሎት ግብዣ ተከትሎ የጀሜሊ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና በሮማ የሚገኘው ቅዱስ ልበ ኢየሱስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ ማህበረሰብ “በዚህ የመከራ እና የስቃይ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍ እና አጋርነት” በተለያዩ የጸሎት ጊዜያት ገልፀዋል።

ከየካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከጀሜሊ ሆስፒታል አገግመው እንዲወጡ በየቀኑ ከቀትር በኋላ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ በሆስፒታሉ ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ጸሎት ቤት ለአንድ ሰዓት የሚቆይ የቅዱስ ቁርባን ስግደት እና የመስዋዕተ ቅዳሴ መርሃግብር እንደሚደረግ ተገልጿል።

በዚህ የምስዋዕተ ቅዳሴ እና ስግደት ወቅት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮ ልዩ ጸሎት የሚደረግ ሲሆን፥ በሮማ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ ከሆስፒታሉ ውጭ ባለው አደባባይ ላይ በሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ሐውልት ፊት ለፊት የመቁጠሪያ ጸሎት ይደረግና ከምሽቱ 11 ሰዓት ላይ በሆስፒታሉ ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚቀርብ ተገልጿል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሁሉም ሰዎች በእነዚህ የጸሎት ጊዜያት በአካል እና በመንፈስ እንዲሳተፉ የተጋበዙ ሲሆን፥ ከሮም ውጭ ሆነው የጸሎት መርሃ ግብሩ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎች የሚከተለውን ጸሎት መድገም ይችላሉ ተብሏል፦

“የዓለም ቤዛ የሆንከው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፣ ሕመማችንን ወደ ራስህ ወስደህ በሕማማትህ መከራችንን የተሸከምክ ጌታ ሆይ፣ ስለታመሙት ወንድማችን (አባታችን) የምናቀርበውን ጸሎታችንን ስማን፣ በሥጋም በመንፈስም ከፍ ከፍ እንዲሉ፣ እንዲበረታቱ ተስፋቸውን አድስላቸው” አሜን።
 

25 Feb 2025, 12:01