MAP

ዋሺንግተን ዲ ሲ ዋሺንግተን ዲ ሲ  (AFP or licensors)

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ ለአሜሪካ ብጹአን ጳጳሳት ስደትን አስመልክተው የላኩትን ደብዳቤ በደስታ መቀበላቸውን ገለጹ

የቺካጎ ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የዩናይትድ ስቴትስ ብጹአን ጳጳሳት የስደተኞችን መብት ለማስከበር እያከናወኑ ያለውን አገልግሎት እንደሚደግፉ የገለጹበትን ደብዳቤ በደስታ በመቀበል፥ ካርዲናሉ የስደተኞችን ክብር መጠበቅ እና ለእነሱ መሟገት በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ውስጥ “በአሁኑ ጊዜ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አጣዳፊ ጉዳይ” መሆኑን ጠቁመዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺኮስን መልዕክት በደስታ እንደሚቀበሉ ከገለጹ በኋላ እንደተናገሩት መልዕክቱ ካቶሊኮች ትክክለኛ ሕሊናቸውን እንዲያዳብሩ እና እንዲጠብቁ ያበረታታል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለአሜሪካ ብጹአን ጳጳሳት በጻፉት ደብዳቤ ላሰሙት ማበረታቻ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው በዚህ ደብዳቤ ላይ የሃገሪቷ ብጹአን ጳጳሳት የስደተኞችን መብትና ክብር ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በደብዳቤያቸው ላይ እንደገለጹት “በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ስደተኞችን በጅምላ ወደሃገራቸው ለመመለስ እየተደረገ ያለውን መርሃ ግብር እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ ቀውስ በቅርብ እየተከታተሉት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ በዚህ ረገድ ክርስቲያናዊ ፍቅር ማንኛውም ሰው አሁን የሚገኝበት ህጋዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ለሁሉም ሰው ክብር እውቅና መስጠትን እንደሚጠይቅ በመግለጽ የብጹአን ጳጳሳቱን ጥረት በማድነቅ አመስግነዋል።

ብጹእ ካርዲናል ኩፒች ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ትንቢታዊ ምስክርነት በጣም እንደሚያደንቁ በመግለጽ፥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቷ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች ክብር መሟገት እና ጥበቃ ማድረግ ዋናው እና አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ ቅዱስ አባታችን ለአሜሪካ ብጹእ ጳጳሳት እና ቤተ ክርስቲያን በግልጽ አስቀምጠዋል።

ስደተኞችን በጅምላ ማፈናቀልን እና እንደ ወንጀለኛ ማየትን በግልጽ ለሚቃወሙት ለአሜሪካ ብጹአን ጳጳሳት ቅዱስነታቸው ላደረጉት ማበረታቻ እንዲሁም በሃገሪቷ ውስጥ ያሉትን ስደተኞች ሰብአዊ ክብር ለማስጠበቅ ሁሉም ብጹአን ጳጳሳት በአንድነት እንዲቆሙ ብጹእነታቸው ላሳዩት ተነሳሽነት ብጹእ ካርዲናል ኩፒች ያላቸውን ምስጋና አጋርተዋል።

“በተለይ ካቶሊኮች ትክክለኛ ሕሊና እንዲያዳብሩ ለመርዳት ያላቸውን ፍላጎት በቁም ነገር እመለከተዋለሁ” ያሉት ካርዲናሉ፥ ይህ ሲሆን እንደ ታማኝ ዜጎች እያንዳንዳችን ፍትሃዊ የሆነ ፍርድ ለመስጠት እንዲሁም በተዛባ ሁኔታ ላይ በተመሰረቱ ፖሊሲዎች ላይ ያለንን ተቃውሞ መግለጽ እንችላለን ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች አክለውም “በዚህ ረገድ አሁን እየሆነ ባለው ነገር ከቀጠለ ቅዱስ አባታችን በትክክል እንደተነበዩት የሃገሪቷ ውድቀት በከፋ ሁኔታ ይጀምርና መጨረሻውም የከፋ ይሆናል” በማለት ገልጸዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከያዙበት ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸውን ስደተኞችን ለመቆጣጠር ሰፊ ጥረት የሚያደርጉበት ተከታታይ ከስደት ጋር የተያያዙ የስራ አስፈፃሚ ትዕዛዞችን እንዳስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን፥ ትራምፕ ከ21 በላይ በሆኑ የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዞች ስደተኞችን በጅምላ ከአሜሪካ ማባረር እና ጉዳያቸውን መከታተልን ጨምሮ የዩናይትድ ስቴትስ የኢሚግሬሽን ስርዓት አንዳንድ ክፍሎችን ለማሻሻል ተንቀሳቅሰዋል።

ብጹእ ካርዲናል ኩፒች በመጨረሻም “የስደት ህጋዊው አሰራር የሰውን ልጅ ወሳኝ የሆነ ሰብአዊ ክብር ፈጽሞ ዝቅ ሊያደርግ አይገባም” በማለት አጠቃለዋል።
 

12 Feb 2025, 14:23