MAP

ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ 

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የ2017 ዓ.ም. የዐቢይ ፆምን አስመልክተው መልዕክት አስተላለፉ

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2017 ዓ.ም. የዐቢይ ጾም መግቢያን በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርባለን፦

የተወደዳችሁ ካቶሊካውያን ምዕመናን

በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትገኙ ሁሉ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ላላችሁ ሰዎች በሙሉ

የእግዚአብሔር አምላክ ጸጋና ሰላም በያላችሁበት ይድረሳችሁ፡-

የ2017 ዓ.ም. የዐቢይ ጾም ስንጾም የዓለማችንን በተለይም የአገራችንን አሁናዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የእግዚአብሔር ምህረት እንዲበዛልን በጾምና በጸሎት ይበልጥ ጠንክረን ካለን ላይ ለሌላቸው በማካፈል ሊሆን ይገባል።

ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንቼስኮስ የፈረንጆቹን 2025 ዓ.ም. የተስፋ ነጋድያን የኢዩቤልዩ ዓመት ብለው ባወጁት ዓመት እንድናደርግ ከሚጠበቁ ዋና ዋና ነገሮች ንስሐ በመግባት ከሰዎችና ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ ግንኙነታችንን ማደስና ማጠንከር፣ መጾም እና መጸለይ፣ የተቸገሩትን መርዳት፤ የፍቅርና የምህረት ሥራዎችን መስራት ስለሆነ እኛም በዚህ የዐቢይ ጾም እነኚህን ተግባራት እንደ አንድ ቤተሰብ በጋራ በአንድ ልብ እና በአንድ ነፍስ በማከናወን እንትጋ። እምነታችን እንዲጠነክር፣ ተስፋችን እንዲለመልምና ፍቅራችን እንዲጸና እንጸልይ እንጹም።

“ከዕለታቱም በአንዱ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ፦ ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር አላቸው፤ ተነሡም። ሲሄዱም አንቀላፋ፥ ዓውሎ ነፋስም በባሕር ላይ ወረደ፥ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበርና ይጨነቁ ነበር። ቀርበውም፦ አቤቱ፥ አቤቱ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ተወም፥ ጸጥታም ሆነ። እርሱም፦ እምነታችሁ የት ነው? አላቸው። ፈርተውም ተደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም፦ እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ የሚያዝ ለእርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? አሉ።” (ሉቃ. 8፡22-25)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እምነት እንዳላቸው ያውቃል፤ ጥያቄው ግን ማዕበል ሲነሳ ጭንቀት በሕይወታችሁ ውስጥ ሲነግስ ለመልሳችሁ እምነታችሁን ለምን አትጠቀሙበትም የት ነው ያለው ማለቱ ነው። እኛም ዛሬ እንደ ግለሰብም ሆነ ማኀበረሰብ ላለንበት ሁናቴ በእምነታችን አማካይነት መልስ ልናገኝለት ይገባል። ችግሩ የኑሮ ውድነቱ፣ ውጣ ውረዱ፣ ለመኖር ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ሁሉ መልስ ልናገኝላቸው የሚገባው ከእምነታችንና ነገሮችን ሊያቀና ከሚችለው አምላካችን በመተማመን ሊሆን ይገባል። የምናመልከው አምላክ ከገዘፉብን አስጨናቂ ነገሮች ይበልጣልና በጸሎታችን እና በጾማችን እምነት ጨምርልን በማለት እንማጸነው።

የአገራችን ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታን ስንመለከት አሁንስ ተስፋችን ማነው እግዚአብሔር አይደለምን (መዝ. 39፡7) የሚያስብሉ ነገሮች እናስተውላለን። የኑሮ ውድነት፤ ራስ ወዳድነት፣ መፈናቀል፣ የሴቶችና የሕጻናት መደፈር፣ የሰላም መደፍረስ፣ ብቸኝነት፣ የሞራል ውድቀት፣ የፈጠረንን አምላክ መዘንጋትና እርሱን አለመፍራት፤ ሕይወትን ከመጋፈጥ ይልቅ መሸሽ፤ በፍርኀትና በስጋት መኖር፤ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለማግኘት ከመልፋት ይልቅ አቋራጭ መንገድ መምረጥ፣ ስለሌላው ስሜት አለመቆርቆር ወይም የራስን ስሜት ብቻ ማዳመጥ…ወዘተ አሁንስ ተስፋችን ምንድን ነው እንድንል ያስገድደናል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆነን እንዴት ነው የምንጾመው የሚል ስሜት ይፈጥርብን ይሆናል፣ ነገር ግን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም፤ ይህም ያልፋል እግዚአብሔር መጥፎውን ታሪካችንን ይቀይራልና ውስጣችን በእግዚአብሔር ተስፋ የተሞላ እንዲሆን እንጹም፣ እንጸልይ።

ለማመን ከባድ ቢመስልም የሰው ልጅ ምግብ ሳይበላ ለሰባ ቀናት፤ ውኃ ሳይጠጣ ለአስር ቀናት ያለ አየር ለስድስት ደቂቃ መኖር ይችላል። ያለ ተስፋ ግን ሊኖር አይችልም፤ ስለዚህ ለመኖር ተስፋ ያስፈልገናል። ተስፋ ሕይወት ነውና ህይወትም ተስፋ። ተስፋ ማለት በየዕለቱ ሊገጥሙን የሚችሉ ሥቃዮችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች መፍትሔ ብቻ ሳይሆን ምንም እንኳ አስቸጋሪ ቢሆንም ሊሆን የሚችለውን በጎ ነገርን መጠበቅ ነው፤ ለዚህም ነው ተስፋችን ህያው፣ ጠንካራ፣ ፅኑና የማይናወጥ መሆን ያለበት። ተስፋ እስካለን ብዙ ነገሮች አሉን። የምንሄድበትን አቅጣጫ የሚያሳየን ካርታ፣ የምንንቀሳቀስበት ኃይል፤ እንዲሁም በርካታ አማራጮች፤ ሺህ መንገዶችና ሊገመቱ የማይችሉ ህልሞች አሉን።

ተስፋ ካለን መሄድ ወደምንፈልግበት ቦታ ግማሽ መንገድ ላይ ደርሰናል ማለት ሲሆን ተስፋ ከቆረጥን ግን ለዘለዓለሙ ጠፍተናል ማለት ነው። ስለዚህ በተስፋ የሰዎችን ክፋት ሳይሆን በውስጣቸው ያለውን ጥሩ ነገር እንፈልግ ስለማይቻል ነገር ከማጉረምረም ይልቅ ማድረግ የሚቻለውን ነገር ለይተን እናውጣ፣ ጨለማን ከመርገም ይልቅ ሻማን እናብራ፤ መቆም በሚመችበት ጊዜ ወደፊት እንጓዝ፤ ተስፋ መቁረጥ የዘጋቸውን በሮች እንክፈት፥ አሳዛኝ ክስተትን በእምነትና በጥንካሬ እንቀበል።

“እናቱና ወንድሞቹም ወደ እርሱ መጡ፥ ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሊያገኙት አልተቻላቸውም። እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ወድደው በውጭ ቆመዋል ብለው ነገሩት። እርሱም መልሶ፦ እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አላቸው።” (ሉቃ. 8:19-21)

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የወንድምነትና የእህትነት መለኪያው ሚዛን ወደ ጎሳ፣ ዘር እና ብሔር ወረደና ተጋብተን እንዳልተዋለድን፣ በኃይማኖት እንዳልተሳሰርን ሆነን ተገኘን። ሰው ራስ ወዳድ ሆነ፤ እኔን ዘሬን/ጎሳዬን/ ማለት ብቻ ሆነ። ምክንያት እየፈለግን በዘር ቆጠራ መለያየታችን አልበጀንም ወደፊትም አይበጀንም። ስለዚህ በዚህ የዐቢይ ጾም ወራት የጸሎታችን ሀሳብ የጾማችን አንዱ ትኩረት ከዚህ ጠባብ አመለካከት ወጥተን ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች መሆናችንን ተገንዝበን የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉ ሁሉ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን፤ እናቶቻችንና አባቶቻችን መሆናቸውን አምነን እንድንቀበል ይረዳን ዘንድ እንማጸነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን አንድነታችንን፣ ቤተሰባዊነታችንን፣ ኢትዮጵያዊነታችንን አክብረንና ተከባብረን ወደን እና ተዋደን በመኖር እንድናጠነክረው ኃይልን እንዲሰጠን በጾምና በጸሎት ከልብ እንለምነው፡፡ የጠባብነትና የዘረኝነት መንፈስ ከውስጣችን ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም ብቻ ነውና (ማር.9፡29)

በተናጠልም ሆነ በጋራ ስንጾም ራሳችንን ከምግብና ከመጠጥ፣ ከሥጋ፣ ከጥሩ ምግብና ከሚያሰክር መጠጥ ስንከለክል መጾማችን እንደሆነ ቢታወቅም እውነተኛ የክርስቲያኖች ጾም የሚያሰኘው ግን የስሜት ሕዋሳቶቻችንም ሲጾሙ ጭምር ነው። ክፉ ከመናገር፣ ከመስማትና ከማየት መታቀብ የጾማችን አካል ነውና።

በዚህ የዐቢይ ጾም ወራት ከላይ በተነሱት ሃሳቦች ብቻ ሳይሆን በሚከተሉትም ርእሰ ጉዳዮች ላይ በመጸለይ እንጹም። እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርገን ራሳችንን በፊቱ ዝቅ በማድረግ እንጹም፤ ተግባራችንን፣ ለአምልኮ ብርታት እንድናገኝ ለእግዚአብሔር የገባነውን ስዕለት እንድናጸና፣ ራስን መቆጣጠር እንድንችል፣ ስለ ኃጢአታችን በማዘን፣ መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድና ለጌታ መምጫ ቀን እንድንዘጋጅ፡ ክርስቲያን ወገኖችን እንዳናሰናክል፣ ልንቋቋመው የማንችለውን ችግር ለመቋቋም! የጌታን ፈቃድ እንድናስተውል የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጠን፣ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲልልን፣ እግዚአብሔር እንዲጠብቀን፤ በመንፈሳዊነት እንድንታደስ፣ መለኮታዊ ኃይልን እንዲሰጠን፣ በአካልና በመንፈስ እንድንፈወስ፣ የእግዚአብሔርን ቁጣ ለማብረድ፣ የእግዚአብሔርን እርዳታ እንድናገኝ፣ እግዚአብሔር እንዳያጠፋንና ቁጣውን ከእኛ እንዲመልስ እግዚአብሔር በመካከላችን ይገኝ ዘንድ፣ የወንጌል አገልጋዮች (አብሳሪዎችን) እንዲሰጠን፣ ወንጌል በመላው ዓለም እንዲሰበክ፣ አገልግሎታችን ፍሬ እንዲኖረው፣ ለአገልግሎት እንቅፋት የሚሆኑትን ነገሮች እንድናስወግድ፤ አጋንንት እንዲወጡ፣ በቤተሰብ መካከል መሰናክሎች እንዲወገዱ፣ ለሌሎች መልካም አብነት እንድንሆን፣ በጋራ እንጹም እንጸልይ። እንዲሁም እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን ጾም እንጹም፤ እርሱም የሚከተለው ነው፦

እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ጾም ምን ዓይነት እንደሆነና በረከቱንም ሲናገር በነቢዩ ኢሳይያስ አማካይነት እንዲህ ይላል “እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቆተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?
የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው፥ ባታንጐራጕርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፣ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል።

እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፥ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል፤ አንተም፦ ሰባራውን ጠጋኝ፥ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ። ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፥ ሰንበትንም ደስታ፥ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፥ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፥ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፥ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ፤ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሮአልና።” (ት. ኢሳ. 58፡ 6-14)

እግዚአብሔር አምላካችንና አባታችን ይህንን በዐቢይ ጾም ወራት የምናቀርብለት ጸሎትና ጾም ተቀብሎ እምነት ተስፋና ፍቅርን አብዝቶ ይስጠን። እርሱ የሚፈልገውን ጾም በሚፈልገው መንገድ በመጾም በምህረቱና በፍቅሩ ይጎብኘን፤ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክልን! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናታዊ አማላጅነቷ ትቁምልን! አሜን!!!


ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር
 

23 Feb 2025, 12:36