የዓለም የመገናኛ ባለሞያዎች የኢዮቤልዩ በዓል እየተከበረ ይገኛል
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ ወይዘሮ ማሪያ ሪሳ ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይቀርባል፦
ተስፋ የሚገኘው ከድርጊት ነው
ምንም እንኳን የሚያስፈራ ቢሆንም እዚህ እናንተ መሃል መገኘት በጣም አስደሳች እና ጥሩ ነገር ነው፥ ወቅቱም በጣም ወሳኝ ጊዜ ነው፥ ይህ የተቀደሰ ቦታ ነው፣ እናም በዚህ በጸጋ በተሞላ እና በጥሞና ጊዜ እንደ ዓለም አቀፋዊ ማህበረሰብ እንድንተሳሰር ለሚያደርጉን እሴቶች ዳግም ቃል የምንገባበት የኢዮቤልዩ በዓልን እንጀምራለን።
ይህ ክስተት የተከናወነው ዓለማችን ጥልቅ የሆነ ለውጥ ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው። የዛሬ 80 ዓመት አከባቢ እንደ እኔ እድለኛ ሆኖ በናዚ እስር ቤት ውስጥ ታሞ ሽልማቱን መቀበል ባይችልም ካርል ቮን ኦሲትዝኪ የተባለ ጋዜጠኛ የኖቤል የሰላም ሽልማት በወሰደበት ዘመን የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መምጣት ለፋሺዝም መፈጠር መንስኤ ሆኖ ነበር። ከብዙ ዓመታት በኋላ ልክ እንደ ሄሮሺማ ቦምብ ሁሉ አሁን ባለንበት የመረጃ ስነ ምህዳራችን ውስጥ የአቶሚክ ቦምብ እንደሚፈነዳ የማንቂያ ደውል ሳሰማ ቆይቻለው።
ሥልጣንን እና ገንዘብን ለማግኘት ሲባል አሁን ባለንበት ዘመን ቴክኖሎጂ ፍርሃት፣ ቁጣ፣ ጥላቻ እና መተማመንን የሚያጠፉ ዘይቤዎችን በመዝራት በሁሉም ዲሞክራሲያዊ ሃገራት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ውስጥ ውስጡን ጉዳትን እያስከተለ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ሃኪም ‘የብቸኝነት ወረርሽኝ’ ብለው የጠሩትን ማህበራዊ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። ጎረቤት በጎረቤቱ ላይ እንዲነሳ፣ የአመጽ ድርጊት እንዲስፋፋ እና አደገኛው ማንነታችን ጎልቶ እንዲወጣ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።
የመጀመሪያው የጥቃቱ ሰለባዎች ጋዜጠኞች ነበሩ፥ ስልጣንን ከፈለክ የእኛን ታማኝነት ሙሉ በሙሉ መጣል አለብህ፥ ይህንን ኖሬበት አይቼዋለሁ፥ የራሴ መንግስት በሰዓት በአማካይ 90 የጥላቻ መልዕክቶችን አስተላልፈሻል በሚል ከሶኛል። ይሄንን ጋዜጠኞችን ለማሰር እንደ ግብአት ይጠቀሙበታል። ከመታሰሬ ሁለት ዓመት በፊት ‘#ማሪያ ሬሳ ትታሰር’ በሚል ጽሁፍ በማህበራዊ ድህረ ገጽ በኩል ከፍተኛ ዘመቻ አድርገውብኛል።
የማይቻል የሚመስለውን በመደጋገም የሚቻል ያደርጉታል።
መጀመሪያ ላይ ተይዤ በዋስ ተፈታሁኝ፥ ዕለቱም በ 2011 ዓ.ም. በቫላንታይን ቀን ላይ ስለሆነ ክስተቱንም መቼም አልረሳውም። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መንግስቴ በእኔ ላይ 10 የእስር ማዘዣ አቅርቧል። የዋስ መብቴን ለማስከበር በርካታ ሥራዎችን ለመቀያየር ተገድጃለሁ። ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ፥ ምን ሊከሰት እንደሚችልም አላውቅም ነበር። ሆኖም ግን በፊሊፒንስ የሚዲያ ባለሙያዎች የተቋቋመው ራፕለር የተሰኘው የዲጂታል ሚዲያ እና እኔ ማድረግ የምንችለውን ያክል አድርገናል።
አሁን ከ 10 ዓመታት በኋላ ከአሥር የወንጀል ክሶች ወደ ሁለት ዝቅ ለማድረግ ችያለሁ። አሁንም ቢሆን ዛሬ እዚህ ፊት ለፊታችሁ መጥቼ ንግግር ለማድረግ የፊሊፒንስ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የጉዞ ፍቃድ መጠየቅ ነበረብኝ፥ በመሆኑም ሙሉ በሙሉ መብት ዬለኝም ማለት ነው። ይህ አሳዛኙ ክፍል ነው፥ ፊሊፒንስ ከገሃነም ወደ ሲኦል ተዘዋውራለች እያልኩ ሁል ጊዜ እቀልዳለሁ፥ ነገር ግን የሚያሳዝነው ነገር በፊሊፒንስ በእኛ ላይ የደረሰው ነገር በዓለም ዙሪያ በጣም በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ጭምር ሲከሰት ማየቴ ነው። በአሜሪካ የተደረገውን ምርጫ ‘የአሜሪካን ፖለቲካ በፊሊፒናዊ ገጽታ’ እንደማየት ነው ብየዋለሁ።
ይህ ኢዮቤልዩ የተከሰተው የዓለም ገጽታ ሙሉ በሙሉ በተቀየረበት ወቅት ነው፥ ይህ ማለት ትክክል የሆነው እንደ ስህተት፣ ስህተቱ ደግሞ እንደ ትክክል በሚታይበት ጊዜ ማለት ነው። ልጅ እያለሁ የህሊና ውሳኔዎችን ስለማድረግ የሚያሳይ አንድ የቆየ ካርቱን ፊልም አስታውሳለሁ። ዬትኛውም ዋና ዋና ሀይማኖት ይሄንን አስተምህሮ አለው፥ ለመዋጋት በጣም ከባድ የሆነው ጦርነት በራስህ ውስጥ ነው። እስልምና ጂሃድ ይለዋል፣ ያ በራስህ ውስጥ ያለው ጦርነት ነው።
ነገር ግን በእኔ ዕድሜ ከሆንክ ይህንን የካርቱን ፊልም ታስታውሳለህ፥ በቀኝህ በኩል፣ ‘አድርግ ግፋበት’ ብሎ የሚገፋፋህ ዲያቢሎስ አለህ፥ በግራህ ደግሞ ስለ ርህራሄ፣ ስለ ሌሎች ሰዎች እንድታስብ፣ ትክክለኛውን ነገር እንድታደርግ እና ደግ እንድትሆን፣ ስለ ወርቃማው ህግ የሚያስታውስ ይህ መልአክ አለ። ራስ ወዳድ እንዳትሆን እየነገረህ ነው፥ ለማካፈል፣ መጥፎ ስሜትህን ለመዋጋት ያስችልሃል። ሁሌም ከአጠገባችን ዲያብሎስ እና መልአክ አለ ማለት ነው። እንግዲህ ማህበራዊ ሚዲያ ያደረገው መልአኩን ከትከሻህ ላይ አውርዶ ዲያብሎስን በማሳደግ በቀጥታ ወደ ነርቭ ስርዓታችን እንዲገባ ያደርጋል።
ቢግ ቴክ የተባሉ ትላልቅ ኩባንያዎች ማህበራዊ ሚዲያን ከግንኙነት መሳሪያነት ወደ የጅምላ ባህሪ ቀያሪ ምህንድስና መሳሪያነት ቀይረውታል። እነዚህ መድረኮች ገለልተኛ ቴክኖሎጂዎች አይደሉም፥ ጥልቅ የስነ-ልቦናዊ ድክመቶቻችንን ለመጠቀም የተነደፉ የተራቀቁ ስርዓቶች ናቸው። ከእኛ ቁጣ እና ጥላቻ ገቢ ይፈጥራሉ፥ ስልታዊ በሆነ መንገድ ልዩነቶቻችንን በማጉላት ለተዛባ አስተሳሰብ እንድንጋለጥ በማድረግ ያለንን ተሳስቦ እና ተቻችሎ የመኖር አቅማችንን በዘዴ ይሸረሽራሉ።
በ 2010 ዓ.ም. የተካሄደው የማሳ-ቹቴስ የቴክኖሎጂ ተቋም ጥናት እንዳመለከተው በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጭ ውሸት ከሌላ ትክክለኛ መረጃ በስድስት ጊዜ እጥፍ በፍጥነት እንደሚሰራጭ የገለጸ ሲሆን፥ ይህም ጥናት የተካሄደው ኤሎን መስክ ትዊተርን ከመግዛቱ በፊት ነበር። አንድ ሚሊዮን ጊዜ ውሸት ከተናገርክ እውነት ይሆናል። ሰዎች ውሸትን እውነት ነው ብለው እንዲያምኑ ካደረካቸው እነሱን መቆጣጠር ትችላላችሁ።
የቢግ ቴክ የንግድ ሞዴል ይህንን ድርጊት ይገፋፋል። ብዙ ጊዜ ተናግሬአለሁ፥ አሁንም እንደገና እናገራለሁ፥ ያለ ትክክለኛ መረጃ እውነት ሊኖርህ አይችልም፥ እውነት ከሌለ እምነት ሊኖራችሁ አይችልም። እነዚህ ሦስቱ ከሌሉ እኛ የጋራ እውነታ የለንም። እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ይቅርና ማንኛውንም ችግር መፍታት አንችልም። የጋዜጠኝነት ሙያን ሊኖረን አይችልም፣ ግንኙነቶች ሊኖረን አይችልም፥ ዲሞክራሲ ሊኖረን አይችልም።
የካፒታሊዝም ሥርዓት የሆነው የንግድ ሞዴል የመረጃ ግላዊነት ተረት በሆነበት፣ እንዲሁም ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ስልተ ቀመሮች እኛን በተቆጣጠሩበት ዘመን በሰው ልጅ ክብር ላይ በመሠረታዊ ክህደት ላይ የተገነባ ነው።
በዚህም ወቅት ሶስት ነገሮች ተከስተዋል፡-
- ነባር አድሎአዊ ድርጊቶችን የሚያባብሱ ኩነቶችን
- ከመረዳት ይልቅ ለግጭት ቅድሚያ መስጠትን እንዲሁም
- ማህበራዊ ትስስር በሚከፍለው መስዋእትነት የሰውን ትኩረት የሚስቡ ነገሮች በመፍጠር ገቢ ማግኘት ተፈጠረ።
ይህ በአጋጣሚ የሚሆን ነገር አይደለም፥ በዓመት ከመቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለእነዚህ ኩባንያዎች የሚያስገኝ ሆን ተብሎ የተሠራ ንድፍ ነው። በጣም አስቸጋሪው ነገር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚከሰተው ነገር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ አይቆይም፥ በሁለቱም ምናባዊ እና አካላዊ ዓለማት ውስጥ የምትኖር አንድ አንተ ብቻ አለህ። ቢግ ቴክ ዓለምን የምናይበት መንገድ እና ስሜቶቻችንን በመቀየር የኛን ስነ ምግባራዊ የአኗኗር ዘይቤያችንን ጠልፎ ፍርሃት፣ ንዴት እና ጥላቻ የነገሰበት የከፋውን ስሜታችንን አነሳስቷል። አሁንም የግለሰብ አመለካከት ይኖረን ይሆን?
አዝማሚያውን ማየት እንችላለን፥ ቪ ዴም የተባለ ተቋም እንደገለፀው ካለፈው ዓመት ጀምሮ 71 በመቶ የዓለም ህዝብ በአሁኑ ወቅት በአምባገነን አገዛዝ ስር እንደሆነ ጠቅሷል። ጨቋኝ መሪዎችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ እየመረጥን ነው። ለመሆኑ የመረጃዎች ታማኝነት ከሌለን እንዴት የምርጫ ታማኝነት ሊኖረን ይችላል? ምስጥ በበላው እንጨት ላይ የቆምን ይመስላል፥ መቼ እንደሚፈርስ አናውቅም።
ባለፈው ዓመት ግን የሆነ ነገር ተለውጧል። ታኅሣሥ ወር ላይ በሩማንያ ሃገር ሩሲያ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች አማካይነት ባደረገችው ጣልቃ ገብነት ምክንያት ምርጫን በመሻር የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች። በክሬምሊን ጣልቃ ገብነት ምክንያት ምርጫውን ሽረዋል። አሁን ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ህብረት ውስጥ የወጣችበትን መንገድ ማሰብ ተገቢ ነው። የምርጫ ተቃውሞዎች በመላው ዓለም እየተካሄዱ ነው። ከቬንዙዌላ እስከ ሞዛምቢክ፣ አልፎም እስከ ጆርጂያ፣ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በከፍተኛ ተቃውሞ የጀመረው እና ከታህሳስ ወር ጀምሮ 60ኛ ቀኑን በያዘው የጆርጂያ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች ተደብድበዋል እንዲሁም ታስረዋል። ጋዜጠኞቹ በእነዚያ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ‘አምባገነኖችን እንዴት መታገል እንችላለን’ በሚል ርዕስ የፃፍኩትን መጽሐፌን ይዘው ነበር። መርማሪ ጋዜጠኛ ሞዚያ አማግሎቤሊ ‘በዝምታ መቆም አልችልም’ በማለት ከእስር ቤት ቆይታዋ ዛሬ 14ኛ ቀኗን የረሃብ አድማ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ለዓመታት ቴክኖሎጂ የዓለምን ደረቅ ምድር በእሳት ያቀጣጠለ ክብሪት መሆኑን ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ መረጃዎችን በማቅረብ አሳይቻለሁ። ‘በፍጥነት ተንቀሳቀስ፣ የተለመዱ ነገሮችን ቀይረህ ሰብረህ ሂድ’ ይላል የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ፥ እናም ቢግ ቴክ ዲሞክራሲን እየሰበረ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ነገሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ፌስቡክ በእውነታዎች ላይ ተስፋ እየቆረጠ መሆኑን አስታውቋል። እውነታውን በማረጋገጫ መንገድ የፈበረከውን በመሰረዝ ላይ ይገኛል። ነገሩ በአንተ ላይ ሊወድቅ በተቃረበ ግድብ ውስጥ ጣት እንደማስገባት ነው። ነገር ግን ውድ ማርክ ሆይ ይህ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ጉዳይ አይደለም፥ ይህ የደህንነት ጉዳይ ነው። አስቡት ይህ አዳራሽ ምንም አይነት የደህንነት እርምጃዎች ከሌለው እና በተበላሹ ነገሮች የተገነባ ቢሆን በማንኛውም ጊዜ በእኛ ላይ ሊወድቅ ይችላል።
ምን ያህል ሰዎች መሞት አለባቸው? በ 2010 ዓ.ም. የተባበሩት መንግስታት እና የሜታ ቡድን እራሳቸውን ችለው ወደ ማይናማር ሄደው ፌስቡክ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም አስተዋጽዖ እንዳደረገ አረጋግጠዋል። ሆኖም ግን ማንም ተጠያቂ አልነበረም።
የበይነ መረብ ጥቃት የገሃዱ ዓለም ብጥብጥ ነው። ይሄንን እኔ በግሌ የተማርኩት ነገር ነው፥ ከጥቂት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለትንሹ የራፕለር ተቋም ለስድስት ጊዜ ያክል የደህንነት ጥበቃዎችን ማበልጸግ ነበረብን። ከማይናማር እስከ ዩክሬን እንዲሁም እስከ ጋዛ እና ሱዳን፣ የበይነ መረብ ጥቃት የእውነተኛው ዓለም ግጭቶችን ያበረታታሉ፥ ሁሉም እርስ በርስ ይደጋገፋሉ። ዚምባብዌ፣ አፍጋኒስታን፣ ኢትዮጵያ እና ሌሎች ብዙ የተረሱ የጦር ሜዳዎችን ጨምሮ ማስታወስ ይቻላል። እነዚህ ጦርነቶች የሚካሄዱት በሚሳኤል እና በታንክ ብቻ ሳይሆን በአልጎሪዝም፣ በሐሰት መረጃ እና እውነትን በማጥፋት እንዲሁም ማህበረሰቡን አመኔታ በማሳጣት ነው።
የኢንፎርሜሽን ጦርነት፣ የጂኦፖለቲካል ሃይል ጨዋታ፣ የእነዚህን የመሳሪያ ስርዓቶች ንድፍ እየበዘበዘ ነው። ግቡ አንድ ነገር እንድታምን ማድረግ አይደለም፥ ግቡ ሁሉንም ነገር እንድትጠራጠር ማድረግ ነው፥ ስለዚህም እርምጃ መውሰድ አትችልም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ሀገር እና ባህል ሳይለይ ሁለት ዋና ዋና የተከሰቱ የህብረተሰብ ስብራት መስመሮች አሉ። ይሄም ፆታ እና ዘር ነው፥ ጥቃቶቹም ብዙ ጊዜ የሚቀጣጠሉት በሃይማኖት ነው። ወደ ሚስዮጂንነት ወይም ሴት ጠልነት የሚለወጠው ፆታዊ አድልዎ፣ እንዲሁም ‘ነጭን የመተኪያ ቲዎሪ’ ተብሎ የሃንጋሪ ህገ-መንግስቶች ውስጥ መንገዱ የተመቻቸለት ዘረኝነትን መጥቀስ ይቻላል። በዜናዎች ላይ ስለ ስደት ወይም የዋጋ ግሽበት ተደርጎ ትሰሙታላችሁ፥ ነገር ግን ጉዳዩ በጥልቀት ከታየ ስለፆታ እና ዘር መሆኑን ትገነዘባላችሁ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት እኛ በራፕለር ውስጥ የምንገኘው የቢግ ቴክ ባዶ ተስፋዎችን ለመገንዘብ በቂ የሆነ ነገር በማግኘታችን የራሳችን ውሳኔ ላይ ደርሰናል፥ ስለዚህ ለምናባዊው ዓለም የህዝብ የቴክኖሎጂ አደረጃጀት መገንባት ጀመርን፣ በዚህም ትክክለኛ የሆኑ ሰዎች ለስልጣን እና ለገንዘብ መጠቀሚያ ሳይደረግባቸው እውነተኛ ውይይት ያደርጉበታል። የማትሪክስ ፕሮቶኮል ውይይት መተግበሪያን ከአንድ ዓመት በፊት አበልጽገን ለቀናል፥ ክፍት ምንጭ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ያልተማከለ ነው። የመረጃ ግላዊነትን በሚደግፉ አገሮች ጥቅም ላይ ይውላል፥ ከእነዚህም ፈረንሳይ እና ጀርመን ይገኙበታል። የእኛ ራዕይ ዓለም አቀፍ የዜና ድርጅቶች ፌዴሬሽንን ማቋቋም ነው። በዚህ ወቅት የምንተርፍበት ብቸኛው መንገድ ነው። የሥራ ባልደረባዬ ፔትሮ ኢስማኬል ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ መናገር ይችላል፥ በኤክስ፣ ፌስቡክ እና ብሉ ስካይ ላይ እንድትሞክሩት ሊንኩን ለጥፌላችኋለሁ።
አሁን በቫቲካን ስለምንገኝ ሶስት ነገሮችን ለመጠቆም እፈልጋለው፡ አንደኛ የቴክኖሎጂው ዓለም ውሸቶችን ነው። ይሄንን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስገናኝ ‘ይህ ከአሥርቱ ትእዛዛት ጋር ይቃረናል’ አልኳቸው። ሁለተኛው ይሄንን የለውጥ ቴክኖሎጂ የሚቆጣጠሩ ሰዎች የአምላክን የሚመስል ኃይል እንዳላቸው ይናገራሉ፥ ነገር ግን ከአምላክ አይደሉም። ትዕቢታቸው፣ ጥበብ እና ትህትና አልባነታቸው ዓለምን ወደ ጨለማ ጎዳና እየወሰዱ ያሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ በእራሳቸው አገላለጽ እና ቃላቶች፣ ያልተጣራ እና የማይታወቅ ኃይላቸው የአምልኮ ሥርዓትን ይመስላል።
ለዚህም ነው ሃይማኖት፣ እምነት፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ላይ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት። ‘አምባገነንን እንዴት መታገል ይቻላል’ በሚል ርዕስ በፃፍኩት መጽሃፌ ውስጥ በህይወት ዘመኔ በጣም የረዳኝን “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም አድርጉ” በማለት በቀላል አገላለጽ የተገለጸውን ወርቃማው ህግ ጠቅሻለሁ።
ይህ በውሸት እየተቀረጸ ባለው ዓለም ውስጥ ድፍረትን እንዳገኝ ረድቶኛል፥ በፍርሃት ጸጥ ማለት ባለብህ ወቅት ለመናገር ድፍረትን ሰጥቶኛል፣ ግድግዳዎች መገንባት ቀላል በሚመስሉበት ጊዜ ድልድዮችን ለመሥራት ድፍረት ሰጥቶኛል፥ እንዲሁም መላው ዓለም በአንተ ላይ የዘመተ በሚመስል ጊዜም ለእውነት ለመቆም ድፍረትን ሰጥቶኛል።
“እኔ ያለሁት እኛ ስላለን ነው” የሚል ሃሳብ ያለው ኡቡንቱ (UBUNTU) የሚለውን የደቡብ አፍሪካ ቃል እወደዋለው። ዛሬ ለብዙ ችግሮቻችን መድኃኒት ነው። የእምነት ማህበረሰቦቻችንን የሚያጠቃልል ሁለንተናዊ እውነት ነው። የአንዱ ህመም የሁሉም ህመም ነው።
ቢግ ቴክ የማንነታችንን መጥፎ ገጽታ ሲያወጣ፥ ኡቡንቱ ግን የእኛ እጣ ፈንታ እርስ በርስ የተገናኘ መሆኑን ያስተምረናል፥ ለእውነት፣ ለፍትህ እና ለሰላም የሚደረገው ትግል የሌላ ሰው ጦርነት እንዳልሆነ እና የኛ የራሳችን፣ በዚህ አዳራሽ ውስጥ ያለ የእያንዳንዱ ሰው ትግል እንደሆነ ይነግረናል።
ስለዚህ ምን ማድረግ እንችላለን? ዛሬ ጠዋት በሰላም ከእንቅልፋችን ስለነቃን ፈጣሪን ማመስገን! እኔ አራት ምክሮች አሉኝ፡-
1. የመጀመሪያው ነገር መተባበር ነው፥ የመረጃ ፍሰቶቹ እርስ በእርሳችን እንድንጋጭ የሚያደርጉትን የኅብረተሰቡን የስብራት መስመሮች ለመት አሁን ላይ መተማመንን ማጎልበት እና ማጠናከር ያስፈልጋል።
2. ሁለተኛው በሞራል ግልጽነት እውነትን መናገር ነው፦ ግፍ ሲፈጸም ዝም ማለት ተባባሪነት ነው። ሥርዓታዊ ዘረኝነት፣ ኢኮኖሚያዊ እኩልነት፣ ወይም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች መሸርሸርን ያመጣል፥ የእምነት ሰዎች ትንቢታዊ ድምፃቸውን መልሰው ማግኘት አለባቸው። የኛን የህዝብ መረጃ ስነ-ምህዳሮች ከሚቆጣጠሩት ከመንግስት ጀምሮ እስከ ቢግ ቴክ፣ እንዲሁም እስከ ሚዲያ ያሉ አካላትን ግልጽነት እና ተጠያቂነትን እንዲሰፍን መጠየቅ ይገባል።
3. ሦስተኛው በጣም ተጋላጭ የሆኑትን መጠበቅ ያስፈልጋል ፡- ጋዜጠኞችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ አክቲቪስቶችን መደገፍ። እዚህ ላይ ጀርመናዊው ማርቲን ኒሞለርን ለመጀመሪያ ጊዜ ከታሰርኩ በኋላ በታላቁ ጋዜጣችን ላይ “መጀመሪያ የመጡት ለጋዜጠኞች ነው፥ ቀጥሎ ምን እንደሚፈጠር አናውቅም” በማለት የገለጸውን አባባል ማስታወስ ተገቢ ነው። የእናንተ አውታረ መረቦች ለተገለሉ ማህበረሰቦች ኃይለኛ ጋሻ ሊሆኑ ይችላሉ። ስደተኞችን፣ በቁጥር አናሳ የሆኑ ሀይማኖቶችን እና ሌሎች አድልዎ የሚደርስባቸውን መደገፍ ያስፈልጋል። የጋራ ንቃት የጥላቻን መደበኛነት ይከላከላል።
4. አራተኛው አቅምህን ማወቅ ነው - ሰላምን መገንባት ለጀግኖች ብቻ የተተወ ጉዳይ አይደለም፥ ውሸትን ለመቀበል እና ለመኖር ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የጋራ ሥራ ነው። ራፕለር ያለ ማህበረሰባችን እርዳታ ሊተርፍ አይችልም ነበር፥ ሁልጊዜም የሰውን ተፈጥሮአዊ መልካምነት ያስታውሰኛል። ሁሉም ሰው አቅም ስላለው የዚህ አስቸጋሪ ማዕበል የለውጥ አካል መሆን ይችላል። ይህ ሃይል ደግሞ በፍቅር የጎለበተ ነው።
ይሄንን ነገር ደግሜ ልንገራችሁ፥ ሁሉም ሰው በመተባበር በሞራል፣ በግልጽነት፣ እና እውነትን በመናገር በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመጠበቅ ያለውን አቅም ማወቅ አለበት።
በአስከፊው ጊዜ እንኳን ተስፋ ተራ ነገር አይደለም፥ ይልቁንም ንቁ፣ የማያቋርጥ እና ስልታዊ ነው። የእምነቶቻችን ባህሎች ለብዙ መቶ ዓመታት የመቋቋም ችሎታን ተሸክመዋል፥ እነዚያን የለውጥ ታሪኮች ማካፈል አለብን።
በመͨረሻም…
አንድ ቲ.ኤስ. ኤልዮት የተባለ ሰው “ያለፈውን ዘመን በአሁኑ ጊዜ” የሚል በጣም የምወደውን አባባል ጠቅሷል። እኔ ሁሌም ለራፕለር ሰራተኞች እንደምለው በአሁኑ ወቅት ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ይኖርብናል፣ ምክንያቱም ከአስር ዓመታት በኋላ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት የምንችለውን ሁሉ እንዳደረግን መናገር እንፈልጋለን እላለሁ።
ብዙ የምንጋራው ያለፈው ህይወታችን አሁን ባለንበት ወቅት የተለያየ ምርጫ ይሰጠናል፥ ይሄም ያለፈውን ጊዜያችንን እንዴት እንደምንመለከት እስከመቀየር ድረስ የወደፊት ሕይወታችንን ይፈጥራል።
በህብረተሰባችን ውስጥ ያሉ ስብራቶችን ለመጠገን መፍቀድ እንችላለን፥ ብሎም እነዚህን እያደጉ ያሉ መከፋፈሎችን ለመፈወስ መስራት እንችላለን። ምክንያቱም አሁን ለማድረግ የምንመርጠው ጉዳይ ወሳኝ ስለሆነ ይህ ጊዜ እጅግ አስፈላጊ ነው።
በዚህ አዳራሽ ውስጥ ብዙዎቻችን ተገኝተናል፥ ስለመጣችሁም አመሰግናለሁ፥ የቅድስት መንበር የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት በቫቲካን አንድ ላይ ስለሰበሰበን እና ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቺስኮስ ጋር ስላገናኘን እጅግ አመሰግናለሁ፥ ሁላችንም በመተባበር አብረን ከሰራን ማዕበሉን ልንገታ፣ ግድቡ እንዳይወድቅ ለመከላከል እና ዓለማችንን ለመፈወስ እንችላለን።