የጥር 18/2017 ዓ.ም የ2ኛው መደበኛ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ንባባ
1. ኢሳያስ 62፡1-5
2. መዝሙር 95
3. 1 ቆሮንጦስ 12፡4-11
4. ዩሐንስ 2፡1-11
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ክፍለ ሀገር በምትገኘው ቃና በሚባል ከተማ ሰርግ ነበረ፣ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች። ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር። በሰረጉ ግብዣ ላይ የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት ኢየሱስን “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ኢየሱስም አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ውሃ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው።
አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል፣ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል” አለው። ኢየሱስ ይህን የተአምራት ሁሉ መጀመሪያ የሆነውን ተአምር በቃነ ዘገሊላ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!
ከዮሐ. 2፡1-11 ተወስዶ የተነበበው የዚህ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ የሠርግ ድግስ ላይ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦ ስላሳየው የመጀመሪያ ተዓምር ይነግረናል።
ይህም የኢየሱስ ክርስቶስን ተልዕኮ በሙሉ የሚያመለክት እና የሚገልጽ ነው። ነቢያትም ‘መሲሁ በሚመጣበት ቀን’ ብለው እንደተናገሩት፥ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያዘጋጃል’ (ኢሳ. 25፡6)። ‘ተራሮች በወይኑ ጭማቂ ይንጠባጠባሉ’ (አሞ. 9፡13)። ኢየሱስ ክርስቶስ ጥሩውን የወይን ጠጅ የሚያመጣው ሙሽራ ነው።
በዚህ የወንጌል ምንባብ ውስጥ ሁለት ነገሮችን እናገኛለን፡- የወይን ጠጅ እጥረት እና ከመጠን በላይ ሆኖ መቅረብ። የወይን ጠጅ እጥረት መኖሩን በማየቷ ማርያም ለልጇ፥ ‘የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም!’ አለችው” (ዮሐ. 2:3)። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ ስድስት ትላልቅ ማሰሮዎችን ሞላ እና በመጨረሻም ወይኑ እጅግ የበዛ እና የሚያምር በመሆኑ የግብዣው ጌታ፥ ‘ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል። አንተ ለምን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል?’ ብሎ ሙሽራውን ጠየቀው። (ዮሐ. 2: 10)
ስለዚህም የእኛ ምልከታ ሁል ጊዜ ጎደሎ ሲሆን የእግዚአብሔር ግን እጅግ የበዛ ነው። ለዚህም የቃና ዘገሊላ ተዓምር አንዱ ምሳሌ ነው። (ር. ሊ. ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ ‘የናዝሬቱ ኢየሱስ’ የመጀመሪያ እትም ገጽ 294)። እግዚአብሔር ሰው ያጣውን እንዴት ይሞላል? ‘እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ’ (ሮሜ 5፡20)። እግዚአብሔር ጨካኝ አይደለም! ሲሰጥ ብዙ አድርጎ ይሰጣል። እግዚአብሔር የጎደለንን በላቀ ብዛት ይሰጣል።
በሕይወታችን ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ‘ወይን ጠጅ’ እንደሌለን እንገነዘባለን። ጥንካሬን ጨምሮ ብዙ ነገሮች ይጎድሉብናል። የሚያንገበግቡን ጭንቀቶች፣ የሚያጠቁን ፍርሃቶች ወይም ክፉ ኃይሎች የሕይወት፣ የደስታ እና የተስፋ ጣእማችንን ይወሰዱብናል ማለት እንችላለን።
በማጣት መካከል እግዚአብሔር እጅግ አብዝቶ እንደሚሰጠን እናስተውል። ይህም ተቃራኒ እና እርስ በራሱ የሚጋጭ ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን በጎደለን መጠን እግዚአብሔር ሁል ጊዜ እጅግ አብልጦ ይሰጠናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለቂያ በሌለው ድግስ ላይ ሊሆን ይፈልጋል።
ስለዚህ የአዲስ ወይን ጠጅ አማላጅ ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ እንጸልይ። በዚህ የኢዮቤልዩ ዓመት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተገናኝተን መደሰት እንድንችል እርሷ ትርዳን።”