MAP

ስብከተ ወንጌልና የደኅንነት ምሥጢር ስብከተ ወንጌልና የደኅንነት ምሥጢር 

ስብከተ ወንጌልና የደኅንነት ምሥጢር

የጌታ የተልእኮ ሥልጣን በእምነት የማደግ ጥሪን ያካትታል፡- ‹‹ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው›› (ማቴ.28፡20) ይላል። ስለዚህ፣ የመጀመሪያው መልእክት ለቀጣይ ሕንፀትና ብስለት ጥሪ የሚያቀርብ መሆኑ ግልጽ ነው። ስብከተ ወንጌል እያንዳንዱን ሰውና እግዚአብሔር ለእርሱ ሕይወት ያለውን ዕቅድ በማስተዋል መቀበልን በሚጠይቅ የዕድገት ሂደት ላይ ያለመ ነው። ሁላችንም በክርስቶስ ማደግ ያስፈልገናል። እያንዳንዳችን በሙሉ ልብ ‹‹ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል›› (ገላ.2፡20) ማለት እንድንችል፣ ስብከት ይህን ዕድገት እንድንመኝ ሊቀሰቅሰን ይገባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህን የዕድገት ጥሪ በዋናነት ከትምህርታዊ ሕንፀት አኳያ ብቻ ማየት ትክክል አይደለም። ጌታ ለፍቅሩ ምላሽ እንድንሰጥ ያሳየንን ነገር ሁሉ ‹‹ከመጠበቅ›› ጋር የተያያዘ ነው። ይህም ማለት፣ ከበጎ ሥራዎች በተጨማሪ፣ ከሁሉ በላይ አዲሱን ትእዛዝ፣ የመጀመሪያና ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠውንና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን በሚገባ የሚገልጸውን ‹‹ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ›› (ዮሐ.15፡12) የሚለውን ትእዛዝ ማክበር ነው። በግልጽ፣ የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች የክርስትናን ግብረ ገባዊ መልእክት ፍሬ ነገር በሚያቀርቡበት ጊዜ ሁሉ ባልንጀራን ስለ መውደድ አስፈላጊነት ተናግረዋል። ‹‹ባልንጀራውን የሚወድ እርሱ ሕግን ፈጽሞአልና… ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍፃሜ ነው›› (ሮሜ፡13፡8፣10)።  ቅዱስ ጳውሎስ የፍቅር ትእዛዝ የሕግ ማጠቃለያ ብቻ ሳይሆን ዋና ዓላማውና ግቡ መሆኑን ሲገልጽ ‹‹ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ተጠቃሎአል፤ ይኸውም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው›› (ገላ.5፡14) ይላል። ጳውሎስ ለማኅበረ ምእመናኑ የክርስትና ሕይወት በፍቅር የማደግ ጉዞ መሆኑን ሲገልጽላቸው፣ ‹‹እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፣ ያትረፍርፍላችሁም›› (1ተሰ.3፡12 ) ይላቸዋል። ቅዱስ ያዕቆብም እንዲሁ ማንኛውንም ትእዛዝ እንዳያጓድሉ ክርስቲያኖችን ‹‹በመጽሐፍ ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ ተብሎ የተጻፈውን ክቡር ሕግ እንዲፈጽሙ›› (ያዕ.2፡8) ያበረታታቸዋል።

በሌላ በኩል፣ ይህ የምላሽና የእድገት ሂደት ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን ስጦታ ተከትሎ የሚመጣ ነው፤ ይህም የሆነው ጌታ በመጀመሪያ ‹‹በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው›› (ማቴ.28፡19) ስላለ ነው። የእርሱ ልጆች የሚያደርገን በነጻ የተሰጠን የእግዚአብሔር ስጦታና የጸጋ ስጦታው ቀደምትነት (ንጽ.ኤፌ.2፡8-9፤1ቆሮ.4፡7) እግዚአብሔርን የሚያስደስትና ለእርሱ ክብር የሚሰጥ ዘላቂ ጽድቅ እንዲኖር ያደርጋል። በዚህ ዓይነት ‹‹እንደ መንፈሱ በሆነ›› (ሮሜ.8፡5) ሕይወት አማካይነት በክርስቶስ እንድንለወጥ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን።

የደኅንነት ምሥጢርና መንፈሳዊ ትምህርት

ትምህርትና ትምህርተ ክርስቶስ ይህን ዕድገት ያግዛሉ። በቅድስት መንበርና በተለያዩ ሰባኪዎች ተዘጋጅተው የወጡ በርካታ የቤተክርስቲያን ሰነዶች አሉን። በተለይ ካቴኬዚ ትራዴንዴ (ትምህርተ ክርስቶስ በዘመናችን) የተሰኘው ሐዋርያዊ ማበረታቻ (1979)፣ አጠቃላይ የትምህርተ ክርስቶስ ማውጫ (1997) እና ሌሎች ይዘታቸው እዚህ ላይ መደገም የሌለባቸው ሰነዶች እንዳሉ ትዝ ይለኛል። እዚህ ላይ ልዩ ጠቀሜታ አላቸው ብዬ የማምናቸውን ጥቂት አጠር ያሉ ሃሳቦች ለማቅረብ እወዳለሁ።

በትምህርተ ክርስቶስ ደግሞ የስብከተ ወንጌል ሁሉ ሥራና የቤተክርስቲያን ተሃድሶ መሠረት መሆን የሚገባውን የመጀመሪያ የደኅንነት አዋጅ መሠረታዊ ሚና እንደገና አግኝተናል። የደኅንነት አዋጅ ሥላሴአዊ ነው።የመንፈስ ቅዱስ እሳት በልሳናት መልክ ተሰጠን፣ እርሱም በሞቱና በትንሣኤው የአብን የማያልቅ ምሕረት በሚገልጥልንና በሚያስተላልፍልን በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ማመን ይመራናል። የመጀመሪያው የደኅንነት  አዋጅ በትምህርተ ክርስቶስ መምህር አንደበት በተደጋጋሚ ሊስተጋባ ይገባል። ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ይወዳችኋል፣ እኛን ሊያድን ሕይወቱን ሰጠ፤ አሁን ደግሞ በየቀኑ ሊያስተምራችሁ፣ ሊያበረታችሁና ነጻ ሊያወጣችሁ ከጎናችሁ ይኖራል›› ይላል። ይህ የመጀመሪያ አዋጅ ‹‹የመጀመሪያ›› የተባለው በመጀመሪያ ስላለና በኋላ የሚረሳ ወይም ሌሎች የበለጡ ነገሮች ሲመጡ የሚተካ ስለሆነ አይደለም። በመሠረቱ የመጀመሪያ የተባለው በተለያዩ መንገዶች ደግመን ደጋግመን መስማት የሚገባን፣ በትምህርተ ክርስቶስ ሂደት በማናቸውም ደረጃና ወቅት በዚህም ሆነ በዚያ መንገድ መስበክ ያለብን ዋና አዋጅ ስለሆነ ነው። በዚህ ምክንያትም ‹‹ካህኑ፣ እንደ ማንኛውም ሌላ የቤተክርስቲያን አባል፣ በዕውቀት ማደግ፣ እርሱ ራሱ ያለ ማቋረጥ ወንጌል ሊሰበክለት ይገባል››።

በትምህርተ ክርስቶስ ውስጥ የደኅንነት አዋጅ የበለጠ ጠንካራ፣ መሠረታዊ፣ ጽኑ፣ ትርጉም ያለውና በጥበብ የተሞላ ነው። ከክርስቲያናዊ ሕንጸት ሁሉ ወደ ደኅንነት ምስጢር ጠልቆ መግባትን ይጠይቃል፤ እርሱም በትምህርተ ክርስቶስ ውስጥ የሚገለጥና ያለማቋረጥ የሚበራ ትምህርተ ክርስቶስ የሚያነሣውን የማንኛውንም ትምህርት ጠቀሜታ በተሟላ ሁኔታ እንድንገነዘብ የሚያደርገን ነው። በማኛውም ሰው ልብ ውስጥ ለሚኖረው የዘላለማዊነት ምኞት ምላሽ መስጠት የሚችል መልእክት ነው። የደኅንነት አዋጅ መሠረታዊነት ዛሬ እጅግ ለሚፈለጉ ለእነዚያ መሠረታዊ ነገሮች አጽንኦት መስጠትን ይጠይቃል። በኛ በኩል ካለው ማንኛውም ግብረ ገባዊና ሃይማኖታዊ ግዴታ የሚበልጠውን የእግዚአብሔርን አዳኝ ፍቅር መግለጽ አለበት፤ እውነትን በግዴታ የሚጭን ሳይሆን ነጻነትን የሚጠይቅ መሆን ይኖርበታል።  አንዳንድ ጊዜ ስብከትን አንዳንድ ጊዜ ወንጌላዊ ከመሆን  ይልቅ ፍልስፍናዊ ወደሆኑ ጥቂት የእምነት ትምህርቶች ዝቅ በማያደርግ ደስታ፣ ብርታት፣ ንቃትና ሚዛናዊነት የሚገልጽ ሊሆን ይገባል። ይህ ሁሉ ከወንጌል ሰባኪ በኩል ለመልእክቱ ግልጽ መሆንን የሚያበረታቱ፣ ቅርበትን፣ ለውይይት ዝግጁ መሆንን፣ ትዕግሥትና የጋለ ስሜትንና የማይፈርጅ መስተንግዶን የመሳሰሉ አንዳንድ አስተሳሰቦችን የሚጠይቅ ነው።

ከጥቂት አሥርት ዓመታት ወዲህ የዳበረው የትምህርተ ክርስቶስ ሌላው ገጽታ መንፈሳዊ ትምህርት ነው። ይህ ትምህርት በመሠረቱ ሁለት ነገሮችን፣ ይኸውም መላውን ማህበረሰብ የሚያካትትና እያደገ የሚሄድ የሕንጸት ልምድንና የክርስትና ትምህርት ነገረ መለኮታዊ ምልክቶች እንደገና ማድነቅን የሚመለከት ነው። ብዙ መምሪያዎችና ፕሮግራሞች በእያንዳንዱ የትምህርት ማህበረሰብ ዕውቀት ላይ ተመስርቶ የተለያዩ ቅርጾች ለሚኖሩት ለመንፈሳዊ ትምህርት ተሃድሶ አስፈላጊነት ገና በቂ ትኩረት አልሰጡም። ትምህርተ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ ስለሆነ ሁልጊዜ በዚያ ቃል ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ ምቹ አካባቢና ማራኪ አቀራረብን፣ ልብ የሚነኩ ምልክቶች አጠቃቀምን፣ በሰፊው የዕድገት ሂደት ውስጥ ማካተትንና የሰውን ማናቸውንም ሁኔታ ከጋራ የመስማትና መልስ የመስጠት ጉዞ ጋር ማዋሐድን ይጠይቃል።

ማንኛውም የትምህርተ ክርስቶስ ዓይነት ‹‹የውበትን መንገድ›› መከተል ይፈልጋል። ክርስቶስን ማወጅ ማለት እርሱን ማመንና መከተል ተገቢና እውነት ብቻ ሳይሆን፣ ችግሮች ቢኖሩም ሕይወትን በአዲስ ውበትና ጥልቅ ደስታ መሙላት የሚችል መሆኑን ማሳየት ማለት ነው። ስለዚህ፣ ማንኛውም የእውነተኛ ውበት መግለጫ ከጌታ ኢየሱስ ጋር የሚያገናኝ መንገድ ነው ሊባል ይችላል። ይህም በእውነት፣ በርህራሄና በውበት መካከል ላለው የማይበጠስ ትስስር አነስተኛ ግምት የሚሰጥ የስነ ውበት ንጽጽርን ከማራመድ ጋር የተያያዘ አይደለም። ይልቁን የሰውን ልብ ለሚነካና ከሙታን ተለይቶ የተነሣው የክርስቶስ እውነትና ርህራሄ በእርሱ ውስጥ እንዲፈነጥቅ ለሚያደርግ ውበት አዲስ ክብር የሚሰጥ ነው። ቅዱስ አጉስጢኖስ እንዳለው፣ ውብ የሆነውን ብቻ ብንወድ፣ የማያልቅ ውበት መገለጫ የሆነውን ሥጋ የለበሰው ወልድ ከሁሉ የበለጠ ተወዳጅ ነው፤ እርሱም በፍቅር ማሠሪያ ወደ ራሱ ይስበናል። ስለዚህ፣ ‹‹በውበት መንገድ›› መታነጽ እምነትን የምናስተላልፍበት አንዱ የጥረታችን አካል መሆን ይኖርበታል። እያንዳንዱ የአካባቢ ቤተክርስቲያን ባለፉት ቅርሶች ላይ በመመሥረት ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የዘመናችንን መገለጫዎች በመጠቀም እምነትን በአዲስ ‹‹የምሳሌዎች ቋንቋ›› ለማስተላለፍ እንዲቻል የስብከተ ወንጌል ጥበብ አጠቃቀምን ማበረታታት አለበት። አዲስ ምልክቶችንና አዲስ ምሳሌዎችን፣ ቃሉን ለመግለጽና ለማስተላለፍ አዲስ ሥጋ እንዲሁም ለሰባኪዎች እምብዛም ጉልህ ያልሆኑ ለሌሎች ግን ማራኪ የሆኑ ያልተለመዱ የውበት ዓይነቶችን ጨምሮ በልዩ ልዩ ባህላዊ ሁኔታዎች ውስጥ ዋጋ የሚሰጣቸውን  የውበት ዓይነቶች ለማግኘት ድፍረት ሊኖረን ይገባል።

በወንጌል የአኗኗር ሁኔታ በእምነት ማደግን የሚያበረታታውን የትምህርተ ክርስቶስ ግብረ ገባዊ ክፍል በተመለከተ፣ የጥበብ ኑሮን፣ ራስን የማብቃትና የማበልጸግን ማራኪነትና ዓላማ ደጋግሞ መግለጽ አስፈላጊ ነው። ከዚያ አዎንታዊ መልእክት አኳያ ያንን ሕይወት የሚጎዳ ክፉ ነገር መጥላታችን በተሻለ መልኩ ግንዛቤ ያገኛል። የአደገኛ ትንቢቶች ባለሙያ፣ እና ማናቸውንም ዓይነት ስጋትና ልዩነት ለማጥፋት የቆረጡ ጨፍጋጋ ዳኞች ከመሆን ይልቅ ፈታኝ ሃሳቦችን የምናቀርብ ተደሳች መልእክተኞች፣ ለወንጌል በተገባ የታማኝነት ሕይወት ውስጥ የሚበራ የመልካምነትና የውበት መጋቢዎች ሆነን መታየት ይገባናል።

NJͭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወንጌል ደስታ በሚል አርዕስት በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለመስበክ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግላን እና ለምዕመናን ይፋ ካደረጉት ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 160-168 ላይ የተወሰደ።

23 Jan 2025, 14:34