የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን የሰብአዊ ቀውሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አስታወቀ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢዎች በሱዳን ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አስጠንቅቀው፥ ብጥብጡ በቀጠለ ቁጥር፣ የምግብ እና ውሃ አቅርቦት በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን አስጠንቅቀዋል።
በተለይም በሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ኤል ፋሸር ከሚገኙት አጠቃላይ የህዝብ መጠን 40 በመቶ የሚሸፍኑት ከ5 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በአስከፊ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 11 በመቶ ያህሉ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተገልጿል።
ደም አፋሳሹ የእርስ በርስ ጦርነት በሱዳን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ያደረሰ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን፥ በጦርነቱ፣ በዳርፉር የደረሰውን የዘር ማጥፋት ጨምሮ፣ በአገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን እንደሞቱ፣ እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን እንዳፈናቀለ ይነገራል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ኤል ፋሸር፣ በተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ሰብአዊ ቀውሱን እጅግ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል ብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በኒው ዮርክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በግጭት እየታመሰች በምትገኘው ኤል ፋሽር ከተማ የቀሩት ሰዎች “ለከፍተኛ የምግብ እና የንፁህ ውሃ እጦት” እንደተጋረጡ ገልጸው፥ የከተማው የውሃ መሠረተ ልማት የጥገና ጊዜ በማለፉ እና በነዳጅ እጥረት ምክንያት መውደሙን ወይም ከስራ ውጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኤል ፋሸር ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. በተቀናቃኝ ሃይሎቹ መካከል በተጀመረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በጣም የከፋ ግጭቶችን ማስተናገዷ የተነገረ ሲሆን፥ ወደ 780,000 የሚጠጉ ሰዎች ከተማዋን እና በአቅራቢያው የሚገኙትን የዛምዛም የተፈናቃይ ካምፖችን ለቀው እንደተሰደዱ እና ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት በያዝነው ዓመት ሚያዝያ እና ግንቦት ወር ላይ ብቻ የተፈናቀሉ መሆኑ ተገልጿል።
ከሦስት አራተኛ በላይ የሚሆኑ የዛምዛም ነዋሪዎች ወደ ታዊላ አካባቢ የተፈናቀሉ ሲሆን፥ በዚያ የሚገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አጋሮቹ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ እየሰሩ እንደሆነ ተነግሯል።
በኤል ፋሸር የተከሰተው የውሃ እና የአካባቢ ንፅህና አገልግሎት መበላሸት ምክንያት ከፍተኛ እና አንዳንዴም ገዳይ የሆነ ተቅማጥ በሚያስከትለው የኮሌራ ወረርሽኝ ተባብሶ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፥ ሱዳን ከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ከ32,000 በላይ ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን ሪፖርት ማድረጓን ተቋሙ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በደቡብ ዳርፉር ግዛት ባለፈው ሳምንት ብቻ ሁለት ደርዘን የሚሆኑ ሰዎች በኮሌራ በሽታ መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቋል።
አቶ ስቴፋን ይሄንን ሰብአዊ ቀውስ አስመልክተው እንደተናገሩት ግጭት እና የመሠረተ ልማቶች መውደም የበሽታው ስርጭት እንዲስፋፋ ማድረጉን እና ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችን ማደናቀፉን አብራርተዋል።
በሱዳን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ባጋጠመበት በዚህ ወቅት የሱዳኑ ሉአላዊ ምክርቤት ሊቀ መንበር ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በመላው አገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲጀመር ማዘዛቸው የተነገረ ሲሆን፥ ዘመቻው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሉን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ ያለመ መሆኑን ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች የተከበበችው ኤል ፋሸር ከተማ ሰብአዊ እረፍት እንድታገኝ ሁለቱ ወገኖች እንዲስማሙ እየጠየቀ ነው ሲሉ የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ማክሰኞ ዕለት ገልጸዋል።
ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. በሱዳን ጦር ሃይሎች (SFA) እና በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸውን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ እስከ አሁን ድረስ ከግጭቱ ብሎም በአከባቢው ከተከሰተው ከባድ የድርቅ እና የጎርፍ አደጋ ለማምለጥ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸው ተገልጿል።