እስራኤል በጋዛ የተኩስ አቁም ንግግር ለማድረግ ወደ ኳታር ልዑካን መላኳ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የእስራኤል መንግስት በጋዛ የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን መልቀቅ ላይ ከሐማስ ጋር በቅርበት ለመነጋገር እሁድ ዕለት ልዑካኑን ወደ ኳታር ለመላክ የወሰነ ሲሆን፥ ባለፈው አርብ ምሽት ሐማስ ለ60 ቀናት የተኩስ አቁም ለማድረግ ለቀረበው ሀሳብ "አዎንታዊ ምላሽ" መስጠቱን እና ለድርድር መዘጋጀቱን ገልፆ እንደነበር ይታወሳል።
ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እስራኤል ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ "አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን" ተቀብላለች ብለው የነበረ ሲሆን፥ በእነዚህ ቀናት ተደራዳሪዎቹ ጦርነቱን ለማቆም እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ወደ 50 የሚጠጉ የእስራኤል ታጋቾች አሁንም ድረስ በጋዛ የሚገኙ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ቢያንስ 20 ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
በዚህ የ 60 ቀናት የእርቅ ስምምነት እቅድ መሰረት በሐማስ የተያዙ 10 በሕይወት ያሉ ታጋቾችን እና የ18 ሰዎችን አስከሬን ለማስለቀቅ በእስራኤል በእስር ላይ የሚገኙትን ፍልስጤማውያን እስረኞችን መልቀቅን ያካትታል ተብሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ሐማስ የኳታር፣ የአሜሪካ እና የግብፅ አሸማጋዮች ያቀረቡት ዕቅድ ላይ "ተቀባይነት የሌለው" ለውጥ ቢያደርግም ግብዣውን መቀበላቸውን እና ተደራዳሪ ልኡካን ወደ ኳታር መጓዛቸውን ገልጿል። በዚህም መሰረት የእስራኤል እና ሃማስ የተኩስ አቁም ንግግር በኳታር ለሁለተኛ ቀን እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ሃማስ ቀደም ብሎ ለእቅዱ አወንታዊ ምላሽ እንደሰጠ እና ለመደራደር መዘጋጀቱን ገልፆ የነበረ ሲሆን፥ ሆኖም አንድ የፍልስጤም ባለስልጣን ቡድኑ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የሚደረገው ድርድር ካልተሳካ ግጭት እንደማይቀጥል ዋስትና ማግኘትን ጨምሮ ሌሎች ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በጋዛ በተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ምክንያት በሕዝብ አገልግሎቶች ላይ አጠቃላይ መስተጓጉሎች እየደረሰ መሆኑን ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት በትንሹ 45 ፍልስጤማውያን መሞታቸው ተዘግቧል። የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ከካን ዮኒስ በስተ ምዕራብ የተፈናቀሉ ቤተሰቦችን የሚጠለሉ ድንኳኖች በደቡባዊው የግዛቱ ክፍል ላይ ኢላማ በማድረግ ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፥ በጋዛ በሐማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቅዳሜ ዕለት እስራኤል በፈጸመችው የአየር ድብደባ በትንሹ 45 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ገልጿል።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በጥር 19 የተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት እርከኖች እንዲኖሩት ሆኖ የተቀረጸ ቢሆንም መጋቢት ወር ላይ እስራኤል በጋዛ ላይ አዲስ ጥቃት በመሰንዘር ከዚህ ቀደም ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት በመፍረሱ የመጀመሪያውን ደረጃ ስምምነት ማለፍ አልቻለም ነበር።
የእስራኤል ጦር ድርጊቱን "ሐማስ የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም፣ ኃይልን ማሰባሰብ እና እንደገና ለማስታጠቅ ያለውን ዝግጁነት መሰረት በማድረግ የተደረገ ቅድመ ድብደባ ነው" ሲል ገልጿል።
በዚህ ስምምነት መሠረት ሁለተኛው ደረጃ ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ፣ በእስራኤል ውስጥ ለታሰሩ ፍልስጤማውያን ምትክ በጋዛ ታግተው የነበሩትን መልቀቅ እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣትን ያካትት ነበር።
በሌላ ዜና የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በደማስቆ ባደረጉት ጉብኝት ሶሪያ እና ብሪታንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማደሳቸው ተነግሯል።