ቫቲካን ለሲኖዶስ የትግበራ ምዕራፍ አዲስ መመሪያ ማዘጋጀቷ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በብጹአን ጳጳሳት ሲኖዶስ የወጣው አዲስ ሰነድ “የሲኖዶሱን ሂደት የትግበራ ምዕራፍ ለመረዳት የሚያስችል የትርጓሜ መመሪያ ቃላትን ለማቅረብ ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፥ ይህ ‘የሲኖዶሱ የትግበራ ምዕራፍ መንገዶች’ በሚል በሲኖዶሱ ተዘጋጅቶ ሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገው ሰነድ ‘በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በጋራ ለመራመድ የሚያስችላቸው የጋራ ማዕቀፍ እንደሚያቀርብ’ ብሎም ‘መላውን ቤተ ክርስቲያን በጎረጎሳዊያኑ በ2020 ዓ.ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተጀመረው እና በጥቅምት 2028 ዓ.ም. ፍጻሜውን የሚያገኘው የሲኖዶስ ሂደት መንፈሳዊ ጉባኤ የሚመራውን ውይይት እንደሚያበረታታ’ ተገልጿል።
የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች እንደተናገሩት የመክፈቻ መንገዶቹ የቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶሳዊ ቅርፅ ተልእኮዋ በሆኑ አገልግሎቶች ላይ መመስረቱን ገልጸው፥ ‘የተጠመቁት ሁሉ ኃላፊነቱን እኩል የሚጋሩበት የሲኖዶሱን ሥራ ተግባራዊ ለማድረግ የሚገፋፋን የዚህ ተልእኮ አጣዳፊነት ነው’ በማለት አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች አዲሱን ሰነድ ያዘጋጀው የሲኖዶስ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት ላይ እንደሚገኝ እና እነሱን ለመስማት፣ ጥረታቸውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ከሁሉም በላይ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚደረገውን ውይይትና የስጦታ ልውውጥ ለማነሳሳት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
‘የማሳያ መንገዶቹ ሰነድ የሚጀምረው የአተገባበሩን ምዕራፍ እና ዓላማዎቹን በማብራራት ነው’ ያሉት ብጹእነታቸው፥ የትግበራ ምዕራፍ ተሳታፊዎችን ከነተግባራቸው እና ኃላፊነታቸው እንደሚገልጽ ጠቁመው፥ የዚህ የሲኖዶስ ጉዞ ዋና ነጥብ ከሆነው ከሲኖዶሱ የመጨረሻ ሰነድ ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ለመጠቆም እና በአፈፃፀሙ ደረጃ መንገዳችንን ለመቅረፅ በሚረዱ ዘዴዎች እና መሳሪያዎች ላይ ምክር ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።
“እነዚህን መንገዶች ለሁሉም እናስተላልፋለን” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥ ‘የሲኖዶሳዊ ጉዞ ዋና ርዕሰ ጉዳይ ለሆኑት ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ በተለይም ለብጹአን ጳጳሳት እና የሲኖዶሳዊ ቡድን አባላት ለሆኑት ሊቃነ ጳጳሳት እና በትግበራው ምዕራፍ ላይ በተለያዩ መንገዶች ለሚሳተፉ ሁሉ እናስተላልፋለን’ ካሉ በኋላ በመጨረሻም፥ ‘ይሄንን የምናደርግበት ዋና ዓላማ የእኛ ድጋፍ እንዲሰማቸው ማድረግ እና አጠቃላይ የሲኖዶሳዊ ጉዞውን የሚገልጸውን የውይይት ባህል እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው’ በማለት አጠቃለዋል።