MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ ከምዕመናን ጋር  ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባደረሱበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ ከምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባደረሱበት ወቅት  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በአመጽ እና በጦርነት ምክንያት ለሚሰቃዩት ጸሎት እንዲደረግላቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ እሑድ ሐምሌ 6/2017 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ግቢ ውስጥ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድርሰዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በጦርነት ምክንያት ስቃይ ለሚደርስባቸው እና ችግር ውስጥ ለወደቁት በሙሉ እንዲጸልይላቸው ጠይቀው፥ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በእምነቱ ምክንያት በጥላቻ የተገደለውን እና ያለፈው ቅዳሜ በባርሴሎና ብጽዕናው የታወጀለትን ወንድም ሊካሪዮን ሜይን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሑዱ ዕለት ካቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ በመቀጥል ባደረጉት ንግግር ሁሉም ሰው ስለ ሰላም እንዲጸልይ እና በጦርነት ምክንያት የሚሰቃዩትን እና የተቸገሩትን በጸሎት ማስታወስ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጥሪያቸውን ያቀረቡት፥ እሁድ ሐምሌ 6/2017 ዓ. ም. ጠዋት በካስተል ጋንዶልፎ በሚገኝ የቪላኖቫ ቅዱስ ቶማስ ቁምስና ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ በመሩትበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ሲሆን፥ ቀደም ሲል ባደረጉት ስብከትም፥ በደጉ ሳምራዊ እና በቁስለኛው ሰው ምሳሌ ላይ በማሰላሰል ሁከት እና ድህነት የአንድን ሰው ሕልምን እና ሕይወትን እንዴት ሊያጠፋ እንደሚችል ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሐዋርያዊ መኖሪያቸው ፊት ለፊት በተዘጋጀው ሥፍራ ላይ ከጠዋቱ አምስት ሰዓት ተኩል ላይ ከደረሱ በኋላ በካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ለነዋሪው ሕዝብ ገልጸው፥ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበልም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።


የብፁዕ ሊካሪዮን ሜይን ምስክርነት

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም የስፔን ከተማ በሆነች ባርሴሎና ውስጥ ቅዳሜ ሐምሌ 5/2017 ዓ. ም. የተፈጸመውን የብጽዕና ማዕረግ ሥነ-ሥርዓት አስታውሰው፥ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በእምነቱ ምክንያት በሕዝባዊ አመፅ በጥላቻ የተገደለውን ወንድም ሊካሪዮን ሜይንም አስታውሰዋል።

ወንድም ሊካሪዮን ሜይ የማስተማር ተልዕኮውን በድሆች መካከል በጋለ ስሜት እና በድፍረት መፈጸሙን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ምስክርነቱ በትምህርት መስክ ለሚሠሩት በሙሉ መነሳሻ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

ለወጣት መሪዎች እና አስተማሪዎች ክብር ሲባል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በትምህርት ዓለም ላይ ያደረጉትን አስተንትኖ በመቀጠል፥ በተያዘው የአውሮፓውያኑ የበጋ ወራት ጊዜያቸውን ከወጣቶች ጋር የሚያሳልፉ ወጣት መሪዎችን እና አስተማሪዎችን አመስግነዋል።

በዚህ አውድ በጣሊያን የተዘጋጀውን የጂፎኒ የፊልም ፌስቲቫልን እንደ አስፈላጊ ተነሳሽነት ጠቅሰው፥ በጣሊያን ሳሌርኖ ግዛት ውስጥ የሚካሄደው የፊልም ፌስቲቫል በየዓመቱ ከመላው ዓለም ዙሪያ የሚመጡ ሕጻናትን እና ወጣቶችን በአንድነት የሚያሰባስብ መሆኑ ታውቋል። ዘንድሮ ሐምሌ 10/2017 ዓ. ም. የሚጀመረው የዚህ ዓመት እትም “ሰው መሆን” በሚለው ጭብጥ ዙሪያ የተዘጋጀ እንደሆነ ታውቋል።

ለጣሊያን ፖሊስ የተደረገ ጭብጨባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሥፍራው ከተገኙት ምዕመናን ጋር ባደርሱት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ማጠቃለያ ላይ ሰላምታ አቅርበው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ ከፖላንድ ለመጡ የሥርዓተ አምልኮ አካዳሚ ስልጠና ተሳታፊዎች ሰላምታቸውን አቅርበው ዓመታዊ ንግደት ለማድረግ ከልዩ ልዩ አገራት ለመጡ ጀማሪ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም መዘምራን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸውቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በተለይም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በነበረው ሳልቮ ዳ አኩዊስቶ ስም የተመሠረተው የቬሌትሪ ፖሊስ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለአገሪቱ እና ለሲቪሉ ማኅበረሰብ በሚያበረክቱት አገልግሎት እንዲጸኑ በማበረታታት በሥፍራው የነበሩት ምዕመናን በአገልግሎታቸው የተሰማቸውን ስሜት በጭብጨባ እንዲገልጹላቸው ጠይቀዋል።

 

14 Jul 2025, 17:22