ር.ሊ.ጳ ሊዮ የሰው ሰራሽ አብርኾት የውይይት ድልድይ መገንባት እና ወንድማማችነትን ማሳደግ አለበት አሉ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሰው ሰራሽ አብርኾት (AI ) ላይ ማዕቀፎችን እና መመሪያዎችን በማዘጋጀት በጋራ ጥቅም ላይ እንዲውል ሐምሌ 03/2017 ዓ.ም መልእክት ገልጸዋል፣ ጉባኤው ከሐምሌ 01 እስከ ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም በጄኔቫ ስዊዘርላንድ እየተካሄደ የገኛል።
"የሰው ልጅ የተፈጥሮ ክብር እና መሰረታዊ ነፃነቶች የጋራ እውቅና ላይ በመመስረት የስነ-ምግባር ግልጽነትን እንድትፈልጉ እና የተቀናጀ የአካባቢያዊ እና የአለምአቀፍ የሰው ሰራሽ አብርኾት (AI) አስተዳደር እንድትመሰርቱ በዚህ አጋጣሚ ላበረታታኝ እወዳለሁ" ሲሉ የቫቲካን ዋና ጸኃፊ በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የተፈረመው መልእክት አስታውቋል።
ጉባኤው በተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (ITU) የተዘጋጀ ሲሆን ከስዊዘርላንድ መንግስት ጋር በጋራ በመተባበር ተካሂዷል። ዝግጅቱ የመንግስት፣ የቴክኖሎጂ ካፓኒ መሪዎች፣ ምሁራን እና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው እና ከ AI ጋር የሚሰሩትን ተሳትፎ ይመለከታል።
ብዙዎች “ሰው መሆን ምን ማለት ነው” በሚለው ላይ እያሰላሰሉ ባሉበት በዚህ “ጥልቅ የፈጠራ ዘመን” ዓለም “በመንታ መንገድ ላይ ነች፣ በሰው ሰራሽ አብርኾት (በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የሚመራውን የዲጂታል አብዮት ትልቅ አቅም እየተጋፈጠች ነው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው አጉልተው ገልጸዋል።
AI የስነምግባር አስተዳደር እና የቁጥጥር ማዕቀፎችን ይፈልጋል
“የሰው ሰራሽ አብርኾት ቴክኒካል ስልተቀመርን (አልጎሪዝም) ብቻ በመጠቀም ከብዙ ሁኔታዎች ጋር ራሱን ችሎ የመላመድ አቅም ሲኖረው፣ የእሱን ስነ-ሰብዕ (አንትሮፖሎጂያዊ) እና ሥነ-ምግባራዊ አንድምታ፣ በጥያቄ ውስጥ ያሉትን እሴቶች እና እሴቶቹን ለመጠበቅ የሚያስፈልጉትን ተግባራት እና የቁጥጥር ማዕቀፎችን ማጤን አስፈላጊ ነው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው አስረድተዋል።
"የሰው ሰራሽ አብርኾት 'AI' ስርዓቶችን በስነ-ምግባራዊ አጠቃቀም ላይ ያለው ኃላፊነት የሚጀምረው እነሱን በሚያዳብሩ፣ በሚያስተዳድሩት እና በሚቆጣጠሩት ሰዎች ነው" ነገር ግን ለተጠቃሚዎች ይህንን ተልዕኮ ማጋራት አለባቸው። AI "በሰው ልጅ ላይ ያተኮረ ትክክለኛ የስነ-ምግባር አስተዳደር እና የቁጥጥር ማዕቀፎችን ይፈልጋል፣ እና ከመገልገያ ወይም የውጤታማነት መስፈርት በላይ ነው" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አጥብቀው ተናግረዋል።
ሰላማዊ ማህበረሰቦችን መገንባት
የቅዱስ አውጎስጢኖስ የ "ሥርዓት ጸጥታ" ጽንሰ-ሐሳብ በመጥቀስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይህ የጋራ ግብ መሆን እንዳለበት እና በዚህም AI "የበለጠ ሰብአዊ ማህበራዊ ግንኙነቶችን ስርዓት" እና "ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ማህበረሰቦችን ለሰብአዊ ልማት እና ለሰው ልጅ ቤተሰብ መልካም አገልግሎት" ማሳደግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
AI የሰውን አስተሳሰብ መምሰል እና ተግባራትን በፍጥነት እና በብቃት ማከናወን ወይም እንደ “ትምህርት፣ ስራ፣ ጥበብ፣ ጤና አጠባበቅ፣ አስተዳደር፣ ወታደራዊ እና ግንኙነት” ያሉ አካባቢዎችን ሊቀይር ቢችልም፣ “የሞራል ማስተዋልን ወይም እውነተኛ ግንኙነቶችን የመፍጠር ችሎታን መድገም አይችልም” ሲሉ ጳጳስ ሊዮ አስጠንቅቀዋል።
የዚህ ቴክኖሎጂ እድገት "የሰው ልጅ እና ማህበራዊ እሴቶችን፣ በንጹህ ህሊና የመፍረድ አቅም እና በሰው ልጅ ሃላፊነት ውስጥ ከማደግ ጋር አብሮ መሄድ አለበት"፥ “AI እንዲዳብር እና ለጋራ ጥቅም እንዲውል፣ የውይይት ድልድይ መገንባት እና ወንድማማችነትን ለማጎልበት ማስተዋልን ይጠይቃል” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሳስበዋል። AI "የሰው ልጅን በአጠቃላይ ጥቅም" ማገልገል አለበት ሲሉም አክለው ገልጸዋል።