MAP

የደቡብ ሱዳን ማህበረሰብ ከቤንቲዩ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ ጋር የደቡብ ሱዳን ማህበረሰብ ከቤንቲዩ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ ጋር 

ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ ደቡብ ሱዳን የወንጌል ሰላም ያስፈልጋታል ማለታቸው ተነገረ

በደቡብ ሱዳን የቤንቲዩ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ ሀገሪቱ በ 2026 ሃገራዊ ምርጫ ለማድረግ እየተዘጋጀች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ደቡብ ሱዳን ላይ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ጠቁመው፥ ህዝቡ ከወንጌል የሚገኘው ሰላምን እና ከሁከት ነፃ የሆነ ህይወትን በድፍረት እንዲቀበል ጥሪ በማቅረብ፥ ቤተክርስቲያን፣ ትምህርት ቤቶች እና የአካባቢ ማህበረሰቦች ወጣቶችን ስለ ሰላም፣ ፍትህ እና እርቅ በማስተማር ረገድ ንቁ ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ደቡብ ሱዳን በሚቀጥለው ዓመት ሃገራዊ ምርጫ ለማድረግ እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት የኮምቦኒ ማህበር አባል የሆኑት ሚስዮናዊው ጳጳስ ብጹእ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ በሀገሪቱ ውስጥ የተስፋ ምልክቶች እንዳሉ ሁሉ፥ በሌላ መንገድ ደግሞ በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮች እየታዩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የውሃ ጉድጓዶች፣ የእንግዳ ማረፊያ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የመሳሰሉ ትናንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ትልቅ ትርጉም ያላቸው ፕሮጀክቶች መከናወናቸው አበረታች ጅምሮች መሆናቸውን ጠቁመው፥ በአንፃሩ ደግሞ “በተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች መተዳደራቸው ብቻ እንደ ጥፋተኛ ያስቆጠራቸው” ሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ የአየር ድብደባን ጨምሮ እንደ አዲስ ዳግመኛ እያገረሸ የመጣውን ብጥብጥ አውግዘዋል።

በ 2013 ዓ.ም. በደረሰባቸው ጥቃት በፅኑ ቆስለው የነበሩት ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ውስጥ ጽንፈኝነት በመስፋፋቱ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በመበራከቱ እና የውይይት ልማድ በመሸርሸሩ ምክንያት ህዝቡ ‘በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ’ ውስጥ እንደሚገኝ አሳስበዋል።

“ከመደማመጥ ይልቅ ጭፍን ጥላቻ፣ ከእርቅ ይልቅ ብጥብጥ ይመረጣል” ሲሉ በላኩት መልዕክት የገለጹት ብጹእነታቸው፥ “ዓላማው አገሪቱን በዘላቂ ግጭትና ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ለማድረግ ይመስላል” በማለት በቁጭት ገልጸዋል።

ለወንጌል ሰላም እና ለሰላማዊ እንቅስቃሴ የተደረገ ጥሪ
የወንጌል ሰላምን በመሰረታዊነት መቀበል እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ብጹእነታቸው፥ ‘ዓለም በኃያላን የጦር ሃይል የሚያቀርበውን ሰላም ሳይሆን በወንጌል እንደ ስጦታ ሆኖ የቀረበውን ሰላም መቀበል ያስፈልገናል’ ሲሉ በማሳሰብ፥ የደቡብ ሱዳን ህዝብ የሰብአዊ ክብርን ለመጠበቅ ብቸኛው መንገድ ‘በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈላጊ’ የሆነውን ከአመፅ ነፃ የሆነ ሰላማዊ መንገድ እንዲመርጡ መክረዋል።

ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን ቃላት በማስተጋባት፥ የግጭት መንስኤዎችን፣ ጭፍን ንግግሮችን፣ ውሸቶችን እና የጥቅም ጉዳዮችን ትክክለኛ መንስኤዎች ለማወቅ አስተዋይ መሆን እንደሚያስፈልግ አሳስበው፥ ሽባ በሆነ እና ምንም ነገር በሌለበት ሃገር ውስጥ ሕይወትን መፈለግ መንከራተት እንጂ ወደ ፊት መጓዝ እንደማይቻል አስጠንቅቀዋል።

የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ሰለባ የሚሆኑት ከሁሉም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መገለላቸው እየበዛ የመጣው እና አቅጣጫውን በሳተው ዓለም ውስጥ እየተጨፈጨፉ የሚገኙት ድሆች እንደሆኑ ገልጸዋል።

“ከእኔ ፊት የቆመው ምስኪን ደሃ ተቀናቃኝ ሳይሆን ወንድሜ ነው” ያሉት ብጹእነታቸው፥ አንዳንድ ጊዜ ይህ ሰው እንደማንኛውም ሰው ተስፋ በመቁረጡ የተነሳ ሊያስቸግር እና ሊያታልል እንደሚችል፥ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ድሃው ወንድም ደካማ እና አደገኛ በሆነ ህይወት ውስጥ ተስፋ መኖሩን ይመሰክራል ካሉ በኋላ፣ “የድሆች ኅብረት በተስፋ ውስጥ ይወለዳል” በማለት ገልጸዋል።

የሰላም ባህልን ለመፍጠር ቤተክርስቲያን ያላት ሚና
ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ ደቡብ ሱዳን እና ቤተክርስቲያኒቷ በይቅርታ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠር የሚችሉ መሪዎች እና “የሰላም እረኞች” እንደሚያስፈልጓቸው ጠቁመው፥ እውነተኛ ሰላም በማህበረሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት መቀየር እና ወጣቱን ትውልድ በሰላም እሴት መቅረጽ እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያኒቱ በዚህ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳላት አበክረው የተናገሩት ብጹእነታቸው “የጦር መሳሪያ መስፋፋትን፣ ወጣቶችን በግዴለሽነት መመልመልን እና ሁሉንም አይነት ግፍ እና ኢፍትሃዊነትን በመቃወም በግልጽ መናገር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ በተለይም አመጽን ትተው ሰላማዊ መንገድን የመረጡ ወጣቶችን ምስክርነት ለሌሎች ምሳሌ እንዲሆኑ ማበረታታት አለብን ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን የእርቅ እና የተስፋ ታሪኮችን እንዲያሰራጩ፣ ብሎም እንደ ውሃ እና ጤና ያሉ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማግኘትን ጨምሮ የሰው ልጅን ሁለንተናዊ ልማት እና ማህበራዊ ፍትህን የሚያበረታቱ ተነሳሽነቶችን እንዲደግፉ ጥሪ ያቀረቡት ብጹእነታቸው፥ የሰላም ባህልን ለመገንባት ትምህርት ቤቶች እና ካቴኪስቶች ያላቸውን የማይናቅ ሚና አስታውሰው፥ ትምህርት ቤቶች ልጆች ስለሰብአዊ መብቶች፣ ሰላም እና ኃላፊነት የሚሰማው ዜግነት የሚማሩበት “የተስፋ ቦታዎች” መሆን አለባቸው ካሉ በኋላ፥ አክለውም ካቴኪስቶች በእምነት እና በወንጌል ላይ የተመሰረተ የእውነታውን አማራጭ እንዲያቀርቡ መጠራታቸውን ገልጸዋል።

የቤንቲዩ ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ በመጨረሻም፣ ‘መንገዱ ረጅም እንደሆነ፣ ነገር ግን ለመጪው ትውልድ ሕይወትና ዕድል የሚሰጥ ብቸኛው መንገድ የሰላም መንገድ መሆኑን’ ገልጸው አጠቃለዋል።

01 Jul 2025, 13:27