ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ፥ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የአምልኮ ሥርዓት የጋራ ኮሚሽንን አመሰገኑ
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል፥ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፥ በቫቲካን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ውስጥ ማክሰኞ ግንቦት 19/2017 ዓ. ም. በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተመረቀውን አዲሱ የግዕዝ ሥርዓት የቅዳሴ መጽሐፍ በማስመልከት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ይህን አዲሱ የግዕዝ ሥርዓት መጽሐፈ ቅዳሴን ለማዘጋጀት ከረጅም ዓመታት ወዲህ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የጋራ ኮሚሽን ሊቃውንትን በማመስገን የ “እንኳን ደስ አላችሁ!” መልዕክት ልከዋል።
ብፁዕነታቸው ለጋራ ኮሚሽኑ አባላት በላኩት መልዕክታቸው፥ አዲሱ የግዕዝ ሥርዓት የቅዳሴ መጽሐፍ ታትሞ ወደ ወደ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንዲደርስ ድጋፍ ላደረጉት፥ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ፥ ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ እና በጎ አድራጊዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርዋል።
ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ በዚህ የምስጋና መልዕክታቸው፥ “የቅዳሴ መጽሐፉ የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት እየተከበረ በሚገኝበት በ2025 ዓ. ም. (እ.ኤ.አ.) በቫቲካን በሚገኘው የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ውስጥ መመረቁ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ብጹዕነታቸው በመጨረሻም፥ “የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በግንቦት ወር አማላጅነቷ ለሁለቱም ሀገራት ሰላምን፣ እንዲሁም አዲስ ለተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቡራኬን እንድትለምን!” በማለት የምስጋና መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
28 May 2025, 10:28